የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የ11 ክልሎች፣ የሁለት ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የፌደራል ተቋማትና ማህበራት ወኪሎችን በህዝባዊ ውይይት መድረኮች በማሰባሰብ ከመድረኮቹ ባለድርሻ አካላት አጀንዳ አሰባስቦ ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡
የምክክር ሂደቱን አካታችነት ይበልጥ ለማረጋገጥ እና የሂደቱን ውጤታማነት ለማሳደግ ሲባል በውጭ ሀገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሂደቱ ውስጥ በማሳተፍ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኙ አንስቷል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ ኮሚሽኑ በበየነ መረብ የታገዘ ውይይት በተለያዩ ጊዜያት ከዳያስፖራ ማህበረሰብ ጋር ሲያደርግ መቆየቱን በመግለጽ፣ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ዙሪያ ገንቢ ሃሳቦችን እንዲሁም አጀንዳቸውን መስጠት መቻላቸውን አመልክቷል፡፡
ኮሚሽኑ ተደራሽነቱን ለማስፋት እና ትርጉም ያለው ተሳትፎን ለማረጋገጥ ሲባል ዲያስፖራው በስፋት በሚገኝባቸው በተመረጡ ሀገራት በአካል ተገኝቶ የተለያዩ የዳያስፖራ ተወካዮችን በአካል አንድ ላይ በማምጣት ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመወያየት መሰረታዊ የሆኑ አጀንዳዎችን እንዲለዩ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብሏል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እ.ኤ.አ ኦገስት 30 ቀን 2025 (ቅዳሜ) በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በሕዝባዊ ውይይት የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡
ስለዚህ፣ ከኦገስት 30 በፊት በግልም ሆነ በየቡድናችሁ እና ተቋሞቻችሁ ሆናችሁ ሀገሪቱ ያለችበትን መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሚረዱ እና ልንመካከርባቸው የሚገቡ መሰረታዊ አጀንዳዎችን እንድትለዩ በአክብሮት እንጠይቃለን ብሏል፡፡
በዚህ መርሃግብር በተለይዩ ምክንያቶች ከሀገራችሁ የወጣችሁና በሰሜን አሜሪካና አካባቢው የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ታዋቂና ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተማሪዎች፣ የልዩ ልዩ ማህበራትና አደረጃጀቶች መሪዎች እንዲሁም ሌሎችም በሙሉ እንድትሳተፉ ኮሚሽኑ ጥሪ ያቀርብላችኋል፡፡
በመሆም ከኦገስት 30 በፊት በሚያመቻችሁ መንገድ በመገናኘት የተቋማችሁን ወይም የማህበራችሁን አጀንዳዎች በውይይት ለይታችሁ፣ በጽሁፍ አደራጅታችሁ ይዛችሁ እንድትመጡ ስንል በአክብሮት እናሳውቃለን፡፡