የኮንፍረስ ቱሪዝም ያልተነካ እምቅ ሀብታችን መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

You are currently viewing የኮንፍረስ ቱሪዝም ያልተነካ እምቅ ሀብታችን መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

AMN-ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም

በመጪዎቹ የጳጉሜ እና የመስከረም ወራት በመዲናችን አዲስ አበባ ለሚካሄዱት የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት፣ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ እና ሁለተኛው የካረቢያን እና አፍሪካ መሪዎች“ካሪኮም” ጉባኤን አስመልክቶ ከሆቴል ኢንዱስትሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ላይ ጠቃሚ ዉይይት ማድረጋቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስስ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልፀዋል።

የአገራት መሪዎችን ፣ የአለም አቀፍ ተቋማት ፣ የአየር ንብረት ተመራማሪዎችን ፣ አለም አቀፍ የሚዲያ አካላትን ጨምሮ ከ 25 ሺህ በላይ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት የአየር ንብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ ባለፉት የለዉጥ አመታት ለዘርፉ ልማት የሰጠነዉን ከፍተኛ ትኩረት ተገቢነት የሚያረጋግጡ ማሳያዎች መሆናቸውንም ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባም ከዚህ ቀደም ከተለመዱ ዉስን ጉባኤዎች በእጥፍ የላቁ አለም አቀፍ ኩነቶችን በስኬት በማስተናገድ ላይ ትገኛለች ፣ ለአብነት በተጠናቀቀዉ የበጀት አመት 150 አለም አቀፍ ኩነቶችን በከፍተኛ ስኬት ያስተናገደች ሲሆን 1.3 ሚሊዮን ያህል ጎብኚዎችንም አስተናግዳለች በዚህም 143 ቢሊዮን ብር ያህል ሀብት ወደ ኢኮኖሚያችን ገቢ ሆኗልም ብለዋል።

ለዚህ ከፍተኛ ዉጤት መመዝገብ አዲስ የተገነቡ ፣ የታደሱ ነባር የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች፣ የከተማችን ነዋሪዎች የእንግዳ ተቀባይነትና ተባባሪነት ፣ የግሉ ዘርፍ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የመንግስት የተናበበ ቅንጅት ፣ ጉልህ ድርሻ ያላቸው መሆኑን አስታውሰዋል።

ጉባኤዎቹ የመዲናዋን አዲስ ገፅታ ፣አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ ረገድ የሚኖራቸዉ አስተዋፆ ጉልህ በመሆኑ ይህንን ግብ ለማሳካት በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜትና የላቀ የአምባሳደርነት ሚና ይበልጥ ተቀናጅቶ መስራቱ እንዲቀጥልም ከንቲባ አዳነች ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review