ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዩክሬን ኔቶን መቀላቀል የለባትም አሉ

You are currently viewing ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዩክሬን ኔቶን መቀላቀል የለባትም አሉ

AMN – ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም

ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ጋር ዛሬ በዋሽንግተን ለመወያየት ቀጠሮ የያዙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከሰዓታት በፊት ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን መቀላቀል የለባትም ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አጋርተዋል፡፡

ትራምፕ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ከፈለጉ ከሩሲያ ጋር የገቡበትን ጦርነት በፍጥነት ማስቆም ይችላሉ አሊያም ያስቀጥላሉ ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ጦርነቱ እንዴት እንደጀመረ ማስታወስ ይገባል ብለዋል፡፡

ከ12 ዓመት በፊት ያለምንም ተኩስ ክሬሚያ ተላልፋ ወደተሰጠችበት የባራክ ኦባማ አስተዳደር መመለስ አያስፈልግም ያሉት ትራምፕ፣ ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን መቀላቀል የለባትም በማለት ጽፈዋል፡፡

ትራምፕ አያይዘውም አንዳንድ ነገሮች ፈፅሞ መለወጥ አይችሉም ሲሉም አክለዋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ዋሽንግተን ከተማ መድረሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ፕሬዚዳንቱ በሀገራቸው ያለው ጦርነት በሚያበቃበት ሁኔታ ላይ ከትራምፕ ጋር ለመወያየት ወሳኝ በሆነው የኋይት ሀውስ ስብሰባ ከበርካታ የአውሮፓ መሪዎች ጋር ይገኛሉ።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review