ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የማርቺንግ ባንድ ፌስቲቫል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደምትሳተፍ የመከላከያ ሰራዊት ስነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደሚካኤል ገለጹ።
በመከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ሰራዊት ስነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደሚካኤል ፌስቲቫሉን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሁሉም ዘርፎች ያለውን ተቀባይነትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማሳደግ ለሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሰራዊቱን አቅምና ልዩ ችሎታ የሚያጎለብቱ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ አንዱና ዋነኛው ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያገኘችውን ተቀባይነት ተከትሎ በዓለም አቀፍ የማርቺንግ ባንድ ፌስቲቫል ተሳታፊ እንድትሆን ከአንድ ዓመት በፊት ጥሪ መቅረቡን አስታውሰዋል።
በዚህም የመከላከያ ኪነ-ጥበባት ዳይሬክቶሬት የማርቺንግ ቡድን በሩሲያ ሞስኮ በሚካሔደው ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሳተፍ አስታውቀዋል።
ሃምሳ አባላት የያዘው ማርቺንግ ቡድኑ ዛሬ ምሽት ወደ ሩሲያ ለሚያደርገው ጉዞ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አብራርተዋል።
ቡድኑ ለሁለት ሳምንታት በሚኖረው ቆይታ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሰራዊት ማርቺንግ ብቃትና አቅም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደሚያስተዋውቅም አንስተዋል።
ፌስቲቫሉ ከማርቺንግ ትርዒት በዘለለ ለሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጨመር፣ ለባህልና ልምድ ልውውጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።