የደመወዝ ማሻሻያውን ተከትሎ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል

You are currently viewing የደመወዝ ማሻሻያውን ተከትሎ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል

AMN ነሐሴ 12/2017

የደመወዝ ማሻሻያውን ተከትሎ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ከመንግስት አመራር መሰጠቱን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ የሚደረግ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ አድርገዋል።

የደመወዝ ማሻሻያው ቋሚ ገቢ ያላቸው የመንግስት ሰራተኞችን የኑሮ ጫና ለማቃለል የተደረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ `ኃይሌ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ መንግስት የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎችና መመሪያዎች እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።

የደመወዝ ማሻሻያው መንግስትን ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት የሚያስወጣ ቢሆንም ለመንግስት ሰራተኛው ኑሮ መሻሻል ቅድሚያ መሰጠቱን እንደሚያሳይ ነው የተናገሩት።

የደመወዝ ማሻሻያው የመንግስት ሰራተኞች ሥራቸውን በአግባቡ በመከወን ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የተጣለባቸውን ድርብ ሃላፊነት እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።

የደመወዝ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ መመሪያ መስጠቱንም አመልክተዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዳሳወቀው በማንኛውም የንግድ እቃ እና አገልግሎት ግብይት ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ ሰው ሰራሽ እጥረት ለመፍጠር ምርት የሚሰውሩ እና አላግባብ የሚያከማቹ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው።

ሚኒስቴሩ በየደረጃው ከሚገኝ የንግድ መዋቅርና ከፍትህ እና ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ የገበያ ማረጋጋት፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በማጠናከር በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ የግብይት ሂደቱ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል የሚደረግ መሆኑንም አመልክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review