የሰዎችን መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ህገ መንግስታዊ መብት ማስጠበቅ የሚያስችል የመረጃ ነፃነት አዋጅ ተዘጋጀ

You are currently viewing የሰዎችን መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ህገ መንግስታዊ መብት ማስጠበቅ የሚያስችል የመረጃ ነፃነት አዋጅ ተዘጋጀ

AMN – ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም

የሰዎችን መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ህገ መንግስታዊ መብት ማስጠበቅ የሚያስችል የመረጃ ነፃነት አዋጅ ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ራሱን ችሎ በተዘጋጀ የመረጃ ነጻነት አዋጅ ዙሪያ ከፌዴራል፣ ክልሎች እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን የሥራ ኃላፊዎችና ህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጋር በአዳማ እየመከረ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በኢፌዲሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 15፤ በአዋጅ ቁጥር 211/1992 የተቋቋመ ህገ መንግስታዊ የዲሞክራሲ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ እንዳሉት፤ በአስፈፃሚ ተቋማት ላይ የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን የመመርመር፣ ጥናት የማድረግ፣ ግንዛቤ የመፍጠር እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ቁጥር ሶስትን የመቆጣጠር ሚና አለው፡፡

የመረጃ ነፃነት ሰብዓዊ መብት መሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና ያገኘው እኤአ በ1946 በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መሆኑን አስታውሰዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት እኤአ በ1948 ባወጣው የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ አንቀጽ 19 ላይ የመረጃ ነፃነት መሰረታዊ ሰብዓዊ መብት መሆኑን መደንገጉን አውስተዋል።

ዩኔስኮ እኤአ በ2024 ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ 34 በአጠቃላይ 139 የዓለም ሀገራት የመረጃ ነፃነት ህግ ማውጣታቸውን ይፋ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም የመረጃ ነፃነት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ሀገር በቀል ህግ ወደ መሆን መሸጋገሩን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን እኤአ በ1993 ከፈረመች በኋላ የሰዎችን መረጃ የመጠየቅ፣ የመቀበልና የማስተላለፍ ነፃነት ተቀላቅላለች ብለዋል።

በዚህም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ማንኛውም ሰው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት መብት እንዳለው መደንገጉን ገልጸዋል።

የመረጃ ነፃነት ድንጋጌውን ለማስፈጸም በመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ዝርዝር ድንጋጌዎች መውጣታቸውን ተናግረዋል።

በአዋጁ ማንኛውም ሰው ከማንኛውም መንግስታዊ አካል መረጃ የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት የሚሰጥ፣ መንግስታዊ አካላት መረጃ አትሞ ማውጣት እንዳለባቸው እንዲሁም በጊዜ በተገደበ ሁኔታ መረጃ የመስጠት ድንጋጌ የያዘ መሆኑ መልካም ጎኖቹ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የመንግስት አካላት ግዴታቸውን ሳይወጡ ሲቀሩ የማስገደጃ ስርዓት በህጉ አለመካተቱ፣ የማይገለጹ መረጃዎች አንቀጾች ለትርጉም የተጋለጡ መሆኑ የአዋጁ ውስንነቶች መሆናቸውን መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመሆኑም የሰዎችን መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ህገ መንግስታዊ መብት ለማስጠበቅ በአዲስ ህግ መተካቱ በመንግስትና በዕንባ ጠባቂ ተቋሙ ታምኖበት ራሱን ችሎ የመረጃ ነፃነት አዋጅ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review