በከተማዋ የሚካሄዱ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤዎች ለቱሪዝም እና የሆቴል ኢንዱስትሪ መልካም ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ባለድርሻዎች ገለጹ‎‎

You are currently viewing በከተማዋ የሚካሄዱ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤዎች ለቱሪዝም እና የሆቴል ኢንዱስትሪ መልካም ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ባለድርሻዎች ገለጹ‎‎

AMN- ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም

‎በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄዱ የሚጠበቁት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ሳምንት፣ 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ 2ኛው የካሪቢያን እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤዎች ከ25 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የሚታደሙባቸው ዓለም አቀፍ ሁነቶች ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሆቴሎች እና ቱሪዝም ኢንደስትሪዎች ዘርፍ ባለድርሻዎች ጋር 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ውይይት አድርጓል።

ተሳታፊዎቹ በመዲናዋ በስፋት እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር እና የወንዝ ዳር የልማት ስራዎች ለሆቴሎች እና የቱሪዝም ኢንደስትሪ ዘርፍ ውጤታማነት አስተዋፅኦው ከፍተኛ መሆናኑን ገልፀዋል ።

‎የግዮን ሆቴሎች ድርጅቶችን ወክለው የመጡት አቶ በረከት መልካሙ፣ በመዲናዋ የተሰሩ የልማት ስራዎችን አድንቀው፣ ለሚመጡ እንግዶች ለማስጎብኘት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

‎በከተማዋ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ሁነቶች እንግዶችን ከማስተናገድ ባሻገር፣ በከተማዋ የሚኖራቸውን ቆይታ ለማራዘም የሚረዱ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የሚያመላክት እንደሆነም ገልፀዋል።

‎ከሆቴል ባለንብረቶች ማህበር የመጡት ወይዘሮ አስቴር ሰለሞን፣ ከዚህ ቀደም በቱሪዝምና ሆቴል ዘርፍ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ይነሱ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ አሁን ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ከተማዋ የማይስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎችን አድንቀዋል።

የተሰሩ ስራዎች ለዘርፉ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ያስታውቃል ያሉት ወይዘሮ አስቴር፣ ቱሪዝም በኮሚሽን ደረጃ መቋቋሙ ትልቅ እምርታ እንዲኖረው የሚያስችል ነው ብለዋል።

‎ከሳንስፖት ሆቴል የመጡት ሳባ ሀይለማርያም በበኩላቸው፣ ከተማችን በዚህ ልክ አምራ እና ንፁህ ሆና እንግዶቻችንም ሲገቡ ሲወጡ እንዳንሳቀቅ ያደረገ ስራ ነው በማለት ገልጸዋል።

በከተማዋ የተሰሩ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች በእንግዳ አቀባበል ላይ ለተሰማራነው ትልቅ ኩራት እንዲሰማን ያደረገ ነው ሲሉም አክለዋል።
‌‎
ከአዲስ አበባ ሆቴል እና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ወክለው የተገኙት አሸናፊ ሙልጌታ በበኩላቸው ፣ አዲስ አበባን ለቱሪዝም ምቹ ያደረጉ እጆችን አመስግነው፣ በሁለት እና ሶስት ዓመታት ውስጥ “ቱሪዝም” ቋንቋችን እንዲሆን ምክንያት ሆኗል ሲሉ ነው የገለፁት።

‎አሁን ላይ በከተማችን ሁላችንም ስለቱሪዝም እና እንግዳ አቀባበል የምናወራበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯልም ነው ያሉት።

በተሰሩ ስራዎች አማካኝነት በከተማዋ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች፣ ለከተማዋ ቱሪዝም እና የሆቴል ኢንዱስትሪ መልካም ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ በምታካሂዳቸው ጉባኤዎች ለሚሳተፉ 25 ሺህ እንግዶች ከዘርፉ ባለሞያዎች ባሻገር ነዋሪዎች የከተማዋ አምባሳደር በመሆን በኢትዮጵያዊነት ባህል እንግዶችን እንዲቀበሉና ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጥሪ ተላልፏል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review