አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሐረር፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃን እና ጅማ ከተሞችን ጨምሮ በ15 ከተሞች የዲጂታል አድራሻ ስርዓትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነዉ

You are currently viewing አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሐረር፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃን እና ጅማ ከተሞችን ጨምሮ በ15 ከተሞች የዲጂታል አድራሻ ስርዓትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነዉ

AMN ነሐሴ 14/2017

በኢትዮጵያ በየከተሞች ያለውን እድገትና መስፋፋት ተከትሎ ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ በቂ አድራሻ ማግኘት አስቸጋሪ ነው።

ሌላው ቀርቶ ችግር ተፈጥሮ ለእርዳታ የሚንቀሳቀሱ የእሳት አደጋ መኪናና ተጎጂዎችን የሚያነሱ አምቦላንሶች ከተጠሩበት ቦታ የሚደርሱት ከብዙ ምሪት በኋላ እንደሆነ ለመታዘብ ይቻላል።

ኢትዮጵያ ችግሩን ለመቅረፍ የዲጂታል አድራሻ ስርዓትን ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገች ይገኛል።

የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ማንኛውም ሰው በቀላሉ አንድን ቦታ ሊረዳው በሚችል መልኩ ለሰዎች ማሳወቅ የሚችልበት መገኛ ተኮር (location) አሰራር ነው።

የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ አግማሴ ገበየሁ በዲጂታል ስርዓቱ አማካኝነት የቢሾፍቱ ከተማ የሙከራ ትግበራ ተጠናቆ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም አገልግሎቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የቢሾፍቱን መልካም ተሞክሮ በመውሰድ ስርዓቱን ወደ ሌሎች ከተሞች የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሐረር፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃን እና ጅማ ከተሞች የአየር ፎቶግራፍ የማንሳት፣ ዳታ ዝግጅት፣ አድራሻ መስጠት፣ የመረጃ ዝግጅት፣ የካርታ ዝግጅቶች እና ከዲጂታል ስርዓት የማስተሳሰርን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች በመገባደድ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የስድስቱ ከተሞች የሙከራ ጊዜ ተጠናቆ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ስራቸው የተጀመረው ኮምቦልቻ፣ ጎንደር፣ አርባ ምንጭ፣ ሚዛን አማን፣ ወላይታ ሶዶ ፣ አዋሽ ሰባት፣ ሃዋሳ፣ ጅግጅጋ እና ድሬዳዋ ከተሞች የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ዝርጋታ በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ነው አቶ አግማሴ የገለጹት።

በአጠቃላይ በተያዘው በጀት በ15 ከተሞች ስርዓቱ ሙሉ ለሙሉ እንደሚተገበር ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ ከከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በዘንድሮው በጀት የ18 ከተሞች የዲጂታል ስርዓት ዝርጋታ ዝግጅት ስራዎች ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙን አመልክተዋል።

አድዋ፣ አምቦ፣ አዲግራት፣ ሽሬ፣ አክሱም፣ መቀሌ፣ ወልዲያ፣ ወልቂጤ፣ ባቱ፣ ቦንጋ፣ ፍቼ፣ ጋምቤላ፣ ጅንካ፣ ከሚሴ፣ ሮቤ፣ ሸገር፣ ወራቤ እና ወሊሶ የዝግጅት ስራ የሚከናወንባቸው ከተሞች ናቸው።

እንደ አቶ አግማሴ ገለጻ፤ የ18ቱ ከተሞች ስራ በ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ እና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ዲጂታል አድራሻ ስርዓት አቅጣጫ ከመጠቆም ባለፈ እቃ ማድረስ (ዲሊቨሪ)፣ አምቡላንስ፣ የኤሌክትሮኒክ ግብይት (e-commerce)፣ መንገዶች፣ መሠረተ ልማቶች እና ሌሎች አገልግሎቶችን በኦን ላይን ተደራሽ ማድረግን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም አብራርተዋል።

በ10 ዓመቱ መሪ ልማት እቅድ 73 ከተሞችን የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review