በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት እና ስራ ፕሮጀክት መርሐ-ግብር ስር ታቅፈው ውጤታማ የሆኑ ማህበረሰቦች፣ በምስራቅ አፍሪካ የዓለም ባንክ ፕራክቲስ ማናጀር ሎሊ አሪባስ ባኑስ እና በባለድርሻ አካላት ተጎብኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት ሎሊ አሪባስ በፕሮጀክቱ ጥሩ ወጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት እና ስራ ፕሮጀክት አስተባበሪ አቶ አንዱዓለም ገሰሰ፣ ፕሮጀክቱ በዘላቂነት ድህነትን ከኢትዮጵያ ውስጥ ለመቅረፍ እየሰራ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ 2.5 ሚሊየን የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት እና ስራ ፕሮጀክት አስተባባሪ ተመስገን ሙሉዓለም (ዶ/ር)፣ በከተማ ደረጃ በ2017 ዓ.ም 259 ሺህ ማህበረሰቦችን በፕሮጅክቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ምክትል ስራ አስፈፃሚና የስራና ክህሎት ጺ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ውቢት ዮሐንስ፣ በክፍለ ከተማው የሴፍትኔት አገልግሎትን በሀገር ውስጥ በጀት ለመሸፈን በተወሰደው እርምጃ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው፣ በፕሮጀክቱ ስር ታቅፈው መስራት ከጀመሩ ወዲህ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት እና ስራ ፕሮጀክት በመላ ሀገሪቱ በ87 ከተሞች ላይ እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በሀብታሙ ሙለታ