የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በሩስያ እና ዩክሬን መካከል ሊደረግ የሚችል ስምምነትን ተከትሎ ለኪየቭ የደህንነት ማስተማመኛ ለመስጠት ጦራቸውን ወደ ዩክሬን ድንበር እንደማይልኩ ተናግረዋል፡፡
ጦርነቱን ለማስቆም ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ የተናገሩት ትራምፕ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል በሚካሄደውን ጦርነት ዙሪያ ስምምነት ላይ ከተደረሰ ለዩክሬን የአየር ላይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት፡፡
በትላንትናው እለት ከፎክስ ኒውስ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፕሬዝዳንቱ፣ ሁለቱ ሀገራት በሚኖራቸው ቀጥተኛ የሰላም ድርድር አሜሪካ ከተዛቢነት ያለፈ ሚና እንደማይኖራት ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ ይህን ያሉት ከሶስት አመታት ተኩል በላይ የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ እና ከአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ጋር ከመከሩ በኋላ ነው፡፡
በዚህ ውይይት ወቅት አውሮፓውያን በዩክሬን ድንበርውስጥ ጦራቸውን ለማስፈር ባቀረቡት ሀሳብ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፑቲን እና የዘለንስኪ የፊት ለፊት ግንኙነት ጥላ እንዳጠላበት ዘገባዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡
የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ፣ ከቀናት በፊት በአላስካ ከተገናኙ በኋላ በፑቲን እና በዘለንስኪ መካከል ቀጥተኛ ንግግር ሊካሄድ እንደሚችል ሲነገር ቆይቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከፑቲን ጋር ለመገናኘት ፈቃደኘነታቸውን ቢያሳዩም ከክሪምሊን እስካሁን ማረጋጋጫ አልተገኘም፡፡
በዚህ ጉዳይ ስጋታቸውን ያንጸባረቁት ትራምፕ “ፑቲን ጦርነቱን ለማስቆም ሙሉ ፈቃደኛ ስለመሆኑ በሚቀጥሉት ሳምንታት እናውቃለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአላስካው ግንኙነት ወቅት ፑቲን ዘለንስኪንን ፊት ለፊት ለማናገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ በማግስቱ የሩስያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ የሰጡት መግለጫ የተስፋ ጭላንጭሉን ያጨለመ ሆኗል፡፡
ሚኒስትሩ፣ በንግግራቸው የመሪዎች ግንኙነት ከመደረጉ በፊት በባለሙያዎች እና በተደራዳሪዎች ደረጃ መቅደም ያለባቸው ጉዳዮች አሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በእነዚህ እና ተያያዥ ውስብስብ ጉዳዮች የተነሳ ጦርነቱን ለማስቆም ከፍተኛ ሚና አለው የሚባለው የዩክሬን እና የሩስያ ሀገራት መሪዎች ግንኙነት ሊራዘም እንደሚችል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
በዳዊት በሪሁን