ከፀጉር የተሰራው የጥርስ ሳሙና

You are currently viewing ከፀጉር የተሰራው የጥርስ ሳሙና
  • Post category:ጤና

AMN- ነሐሴ14/2017 ዓ.ም

የለንደን ኪንግ ኮሌጅ ተመራማሪዎች የጥርስ መቦርበርን ይቀርፋል ያሉትን ከጸጉር የተሰራ የጥርስ ሳሙና አስተዋውቀዋል፡፡

በፀጉር፣ በቆዳ እና ለሻምፑ መስሪያነት ከሚያገለግለው ሱፍ ላይ ከሚገኝ “ኬራቲን” ከተሰኘው ፕሮቲን የሚዘጋጀው የጥርስ ሳሙና ያለ ጊዜ የሚቦረቦሩ ጥርሶችን ጉዳት ለመከላከል እና ባሉበት እንዲያገግሙ ለማድረግ እንደሚያስችል ነው የተሰማው፡፡

የዚህ አዲስ ግኝት ባለቤት ከሆኑ ተመራማሪዎች መካል አንዱ ዶክተር ሼሪፍ ኤልሻርካዊ፣ “ከፍተኛ ህመም የሚፈጥረውን የጥርስ መቦርቦር ለመከላከል የሚያስችለው ይህ ግኝት በዘርፉ ጨዋታ ቀያሪ ነው” ብለውታል፡፡

የጥርስ ሳሙናው በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠር የጥርስ መቦርቦርን ባለበት በማስቆም ሰዎች ጉዳት እንዳጋጠማቸው እንኳን ሳያውቁ ፈውስ የሚሰጥ ነው ተብሎለታል፡፡

ኬራቲን የተሰኘው ፕሮቲን ከምራቅ እና ከሌሎች ማዕድናት ጋር ሲዋሀድ የጥርስ መቦርቦር የሚያጋጥመውን የታችኛውን የጥርስ ክፍል ጥንካሬ ለማዳበር እንደሚረዳ ነው ተመራማሪዎቹ የገለጹት፡፡

ሰዎች የጥርስ ሳሙናውን ቀን በቀን በመጠቀም አልያም ጥርሳቸውን ቀብተው በማቆየት ብቻ በሽታን መከላከል እንደሚያስችል መገለጹን የዘገበው ስካይ ኒውስ ነው፡፡

የመጀመሪያ የጥራት ሙከራን በተሳካ ሁኔታ ማለፍ የቻለው ከጸጉር ይሰራል የተባለው የጥርስ ሳሙና፣ ሁለተኛውን የምርምር እና የጥራት ደረጃ ማለፍ ከቻለ በቅርቡ ወደ ገበያ እንደሚገባም ተነግሯል፡፡

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review