የዝምባቡዌ መንግስት የፋይናንስ ሚኒስቴር ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ በመገኘት የልምድ ልውውጥ አደረገ

You are currently viewing የዝምባቡዌ መንግስት የፋይናንስ ሚኒስቴር ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ በመገኘት የልምድ ልውውጥ አደረገ

AMN- ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን በተገኙበት፣ በከተማዋ አጠቃላይ ዘርፈ- ብዙ የልማት ስራዎች እና የመጡ ለውጦች ላይ ለልዑካን ቡድኑ የልምድ ልውውጥ አድርጓል፡፡

በሁለቱ እህትማማች ሀገራት በተደረገው ውይይት ከተማ አስተዳደሩ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ መዲናዋ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መቀመጫ እንደመሆኗ፤ የዜጎችን ህይወት ለመለወጥና በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ምርጥ ከተማ እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ስራዎች በመሰራታቸው ለውጦች መመዝገባቸው ተገልፃል፡፡

ለእነዚህ ውጤቶች መሳካትም የመንግስት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ወሳኝ ሚና መጫወቱ ተመላክቷል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ልምድ ከቀሰመባቸው ጉዳዮች ውስጥም፣ የአመራር የመሪነት ብቃት መኖር፣ ግልፅ፣ የጠራና ሊያሰራ የሚችል እቅድና የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፣ ተግባቦት በመፍጠር ህብረተሰቡን የልማቱ ባለቤት በማድረግ በቅንጅት መስራት ተጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም ተዓማኒነትን ማስረፅ እና በልማቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መቻል፣ የከተማዋን የገቢ አቅም በማሳዳግ ሀብትን አሟጦ መጠቀምና ለታለመለት ዓላማ ማዋል፣ የስራ ባህል መቀየርና የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማጠናከር ለከተማዋ ፈጣን እድገትና ተጨባጭ ለውጥ መመዝገብ ምክንያት መሆናቸውን የልዑካን ቡድኑ ልምድ የቀሰመበት መሆኑ ታውቋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ላደረገላቸው መልካም አቀባበል እንዲሁም ስላካፈላቸው ልምድና ተሞክሮ ልዑካን ቡድኑ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ሁለቱም ሀገራት የሀገራቸውን እድገት እና የህዝባቸውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የነበራቸውን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ልምድ በመለዋወጥ እንደሚሰሩ መግለፃቸው ተመላክቷል፡፡

ከውይይቱ በኋላም የልዑካን ቡድኑ በከተማዋ የተሰሩ እና እየተሰሩ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review