ለመንግስት ሰራተኛው የተደረገውን የደሞዝ ማሻሻያ ተከትሎ የንግዱ ማህበረሰብ ካልተገባ የዋጋ ጭማሪ በመቆጠብ በመተሳሰብ ሊሰራ እንደሚገባ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
መንግስት የሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያስተላለፈውን የደሞዝ ማሻሻያ ውሳኔ ተከትሎ ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፤ የደሞዝ ማሻሻያው ለሰራተኛው መነሳሳትን የሚጨምርና ለስራ የሚያተጋ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የደሞዝ ማሻሻያው የመንግስት ሰራተኛው የኑሮ ውድነቱን ለማቋቋም እንደሚረዳ የተናገሩት የመዲናዋ ነዋሪ አቶ መስፍን ሚዛና፣ ማሻሻውን ተከትሎ የንግዱ ማህበረሰብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርግ ከሆነ የመንግስትን ጥረት ዋጋ እንደሚያጣ ሊያደርገው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
አቶ መስፍን አክለውም፣ ይህንን ማሻሻያ ተከትሎ መንግስት የገበያ ማረጋጋት እና በንግዱ ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ቢያደርግ የነዋሪውን የኑሮ ክብደት እንደሚያቃልል ገልፀዋል፡፡
ወጣት ነፃነት ታምራት በበኩሏ፣ የደሞዝ ጭማሪው ጥሩ ሆኖ፣ መንግስት በቤት ኪራይ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ቢቀጥል ብላለች፡፡

ማሻሻውን ተከትሎ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የዋጋ ጭማሪ፤ አልፎም ሸቀጥን በመደበቅ የኑሮ ውድነቱ ላይ አስተዋፅኦ በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ ቢወሰድ የምትለው ወጣቷ፣ ህብረተሰቡም መሰል ተግባራት ላይ የሚሳተፉ ነጋዴዎችን በመጠቆም ለገበያ መረጋጋት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቃለች፡፡
ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ አቶ ሲሳይ በፍቃዱ በበኩላቸው፣ የንግዱ ማህበረሰብ የጭማሪው ተጠቃሚ የመንግስት ሰራተኛ የራሱ አካል፣ ወገኑ እንደሆነ በመገንዘብ በመተሳሰብ መስራት አለበት ብለዋል፡፡

ለአንድ ሃገር፣ ለአንድ አላማ የሚሰራው ሰራተኛውና የንግዱ ማህበረሰብ ጭማሪውን አግዝፎ ሳያይ በመተጋገዝ መቀጠል እንዳለበትም አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡
መተሳሰብ የኢትዮጵያዊያን ባህላችን መሆኑን ባለመዘንጋት መጓዝ አለብን የሚሉት ደግሞ ሌላው የመዲናዋ ነዋሪ አቶ ሙላቸው ፊሊጶስ ናቸው።
አቶ ሙላቸው ገዢ ከሌለ ሻጭም እንደማይኖር በማመላከት ህብረተሰቡ በሁሉም ዘርፍ ተሳስቦ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የደሞዝ ማሻሻያው የስራ መነሳሳትን እንደሚጨምር የገለፁት አቶ ፊሊጶስ፣ መንግስትም ይህንኑ ማሻሻያ ተከትሎ በንግዱ ላይ ክትትል እና ቁጥጥር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሊያት ካሳሁን