የሲሚንቶ ግብይትን ለማረጋጋት በተወሰዱ የአሰራር ማሻሻዎች አዲስ አባባ በሚገኙ አከፋፋዮች ዘንድ ቀደም ሲል በ 2 ሺህ 400 ብር ሲሸጥ የነበረዉ የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ ወደ 1 ሺህ 100 ብር ዝቅ ማለቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ግብይት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሊቁ በነበሩ እንደገለጹት፣ አሁን ላይ የሲሚንቶ ንግድ በተጨባጭ የተረጋጋው በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የመጀመሪያው አዳዲስ ፋብሪካዎች ጭምር ወደ ምርት በመግባታቸው በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ማስቻሉ እንደሆነ እና በሲሚንቶ ግብይት ሥርዓት ላይ ማሻሻያዎች መደረጋቸው እንዲሁም ዋጋውም ገበያ መር እንዲሆን መወሰኑ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በኢስት አፍሪካ ናሽናል ዲስትሪቢዩሽን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አሸናፊ መለሰ በበኩላቸው፣ ለሚ እና ድሬዳዋ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የገበያውን ከ42 በመቶ በላይ ፍላጎት መሸፈናቸውን አንስተዋል።
ይህን ተከትሎም የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ በአዲስ አባባ በሚገኙ አከፋፋዮች ዘንድ ቀደም ሲል ከነበረበት 2 ሺህ 400 ወደ 1 ሺህ 100 ብር ዝቅ ማለቱን እና የተረጋጋ ግብይት መዘርጋቱን አመላክተዋል።
ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ በቀን 150 ሺህ ኩንታል እያመረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሐዋሳ፣ አዳማ እና ጅማ ምርቱን በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ዲፖዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
በቂ ምርት ወደ ገበያ ማቅረብ በመቻሉ ግብይቱን ከማረጋጋት በተጨማሪ የግንባታው ዘርፍ እንዲነቃቃ ማስቻሉን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡