በበጀት አመቱ 200 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦች እና መድሀኒቶች መወገዳቸው ተገለፀ

You are currently viewing በበጀት አመቱ 200 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦች እና መድሀኒቶች መወገዳቸው ተገለፀ

AMN-ነሀሴ 15/2017 ዓ/ም

በበጀት አመቱ 200 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ በህገ ወጥ መንገድ የተመረቱ፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው፣ በአያያዝ ጉድለት የተበላሹ ምግቦች፣ የፅዳት እና የማስዋቢያ ግብአቶች እና መድሀኒቶች ለህብረተሰቡ ሳይሰራጩ መያዙን እና ማስወገዱን የአዲስ አበባ ከተማ የምግብ እና መድኃኒት ባለስልጠን አስታውቋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የ2017 በጀት ዓመት የህብረተሰቡን ጤና ሊያውኩ የሚችሉ ምርቶች ሊያስወግድ የቻለው በመደበኛ ቁጥጥር፣ የሁነት ተኮር ቁጥጥር፣ በልዩ ስጋት የተለዩ የቁጥጥር ስራዎች እንዲሁም በአዲሱ ሪፎርም በተደራጀው የኢንተለጀንስ ስራ አማካኝነት መሆኑ ተገልጿል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበሩ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ባለስልጣኑ የህብረተሰቡን ጤና የሚያውኩ ግብአቶችን ተቆጣጥሮ ከማስወገድ በተጨማሪ፣ የከተማውን እድገት የሚመጥን ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለህብረተሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በጥራትና በፍጥነት ከመስጠት ባሻገር የቅሬታና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ፈጥኖ በማረም ለዜጎች የህይወት ዋስትና መስጠት እንደሚገባም አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ባለስልጠን ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙሉ እመቤት ታደሰ በበኩላቸው፣ መዲናዋ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወንባት መሆኑን ጠቅሰው፤ ደረጃውን የጠበቀ ምግብና መድኃኒት በማቅረብ ስሟን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በተሠራው ሥራም በበጀት አመቱ 200 ሚሊዮን ብር የሚገመት በህገወጥ መንገድ የተመረቱ፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው፣ በአያያዝ ጉድለት የተበላሹ ምግቦች፣ የፅዳት እና የማስዋቢያ ግብአቶች እና መድሀኒቶች ለህብረተሰቡ ሳይሰራጭ መያዙን እና መወገዱን ዋና ስራ አስኪያጇ አብራርተዋል፡፡

ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኝዎች ተስማሚ የሆነ፣ ጤናማና ምቹ አገልግሎት መስጠት ሆቴሎችና ጤና ተቋማት እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት ሰጥተውም ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት አገልግሎት አሰጣጡን በኦንላይን ለመስጠት በተደረገው ጥረት የሙያ ፍቃድን በመስጠትና በማደስ እንዲሁም ጤናን የሚያውኩ የተበላሹ ምግቦችን በማስወገድና ሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን መድሃኒቶች እና ምግቦችን ለገበያ በሚያቀርቡ ተቋማት ላይ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት፡፡

በመርሀ ግብሩ በበጀት አመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት እውቅናና ሽልማት የተሰጠ ሲሆን የተቋሙ ሰራተኞች የደንብ ልብስም ተዋውቋል፡፡

በአለኸኝ አዘነ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review