በውጭ ሀገራት በሚፈጠሩ የስራ ዕድሎች ዜጎች መብትና ደህንነታቸው ተጠብቆ የሚሰሩበት የቴክኖሎጂ አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፍ ሥራ ድርጅት ትብብር የበለጸገው ”ለመንገዴ” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ይፉ ሆኗል።
በዚሁ ጊዜ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ነቢሃ መሐመድ፤ የውጭ ሀገራት የሥራ ዕድል ስምሪት ሥርዓትን የሚያዘምኑ የማሻሻያ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች ዜጎች በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት መብትና ደኅንነታቸው ተጠብቆ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት መፈጠሩን ገልጸዋል።
በራስ አቅም የበለጸገው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መር ሥርዓትም የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አገልግሎትን በማዘመን ዜጎች በመዳረሻ ሀገራት የሚያጋጥማቸውን እንግልት መቅረፍ እንዳስቻለ አስታውቀዋል።
በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው ”ለመንገዴ” የሞባይል መተግበሪያም ዜጎች የሥራ ስምሪት ከመውሰዳቸው በፊት የቅድመ ጉዞ ዝግጅት የሚያደርጉበትን ጠቃሚ መረጃ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የሥራ ስምሪት የሚወስዱ ዜጎችም መብትና ግዴታ እንዲሁም የአሰሪና ሠራተኛን የሥራ ግንኙነት ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑን አብራርተዋል።
በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት የወሰዱ ዜጎችም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ማህበረሰባቸውን በመቀላቀል የራሳቸውን ሥራ መጀመር የሚችሉበት ጠቃሚ መረጃ የሚሰጥ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የማሰልጠኛ ተቋማትና ምርመራ የሚሰጥባቸው የጤና ተቋማትንና የሥራ ስምሪት መዳረሻ ሀገራትን የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስል ቢሮዎች አድራሻ ያሳያል ብለዋል።
የሞባይል መተግበሪያው ዜጎች በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ችግር ቢገጥማቸው ለሚመለከተው ኣካል ጥቆማ መስጠት በሚችሉበት አግባብ መበልጸጉን ማስረዳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዜጎች መብትና ደህንነታቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገር ከሚፈጠሩ ሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።