ተማሪዎችን በማሳለፍ ምጣኔ ዝቅተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ 700 ያህል ትምህርት ቤቶች ጥናትን መሰረት ያደረገ ድጋፍ እንደሚደረግ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

You are currently viewing ተማሪዎችን በማሳለፍ ምጣኔ ዝቅተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ 700 ያህል ትምህርት ቤቶች ጥናትን መሰረት ያደረገ ድጋፍ እንደሚደረግ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

AMN ነሐሴ 15/2017

የትምህርት ሚኒስቴር ”ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በሀዋሳ እያካሄደ ነው።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በወቅቱ እንደገለጹት፥ እንደሃገር ያጋጠመውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን የሚያስችሉ አዳዲስ ሪፎርሞች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

ባለፉት ሁለት አመታት በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የተከናወኑ ተግባራት የዘርፉን የፋይናንስ አቅም በማሳደግ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ጉልህ ሚና እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ጨምሮ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና የመምህራንን አቅም የማሳደግ ስራ በትኩረት ተከናውኗል ብለዋል፡፡

በቀጣዮቹ ዓመታትም የተጀመረውን የንቅናቄ ስራ በማጠናከር ህብረተሰቡን የጉዳዩ ባለቤት ማድረግና የፋይናስ አቅምን በማሳደግ ለውጡን ለማስቀጠል በቅንጅት እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

የትምህርት መረጃ አያያዝ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ ማገዝ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆን አመላክተዋል።

ተማሪዎችን በማሳለፍ ምጣኔ ዝቅተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ 700 ያህል ትምህርት ቤቶች ጥናትን መሰረት ያደረገ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች የተጀመረው የምገባ ፕሮግራም አበረታች መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፥ ፕሮግራሙ ፍትሃዊ ትምህርት ለሁሉም ለማድረስ የተያዘው ግብ የሚሳካበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ የክልሎች የ2017 አፈጻጸም፣ የቀጣይ ዓመት እቅድና አዳዲስ ደምቦች ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን የአጠቃላይ ትምህርት መረጃ ስርዓት ማስተዋወቅና በአዳዲስ ደምቦች ላይም ውይይት እንደሚደረግ ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review