ለበርካቶቻችን ስም መጠሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ስም ከመጠሪያም በላይ ነው፡፡ ሁለት ጓደኛሞች እንቆቅልሽ እየተጫወቱ ነው፤ አንደኛው እንዲህ ብሎ ጠየቀ፡- “አባቴ የሰጠኝ ወንበር ብሞት” የማይሰበር፤ መላሽ፡- ትንሽ አሰብ ካደረገ በኋላ “ስም” ሲል መለሰለት፡፡ አዎ፣ ስም በአካል ስንኖር መጠሪያ ስናልፍ ደግሞ እንደየ ምግባራችን መጠሪያ ነው አይደል የሚባለው፡፡
የበርካቶቻችን ስም ሲወጣልን እኛ ፈቅደን አሊያም መርጠን አናወጣውም፡፡ ይችን ዓለም ስንቀላቀል ወላጆች ምኞታቸው፣ ህይወታቸውን እንዲሁም ሃገራዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታና ክስተትን መነሻ አድርገው ነው ስም የሚያወጡልን፡፡
ታዲያ ስም ይወጣል ከቤት ይቀበላል ጎረቤት እንደሚባለው ስማችን ከመጠሪያ አልፎ ምግባራችንንና የእኛን ማንነት ስናስብም በስማችን እኩል እየተገለፀልን እስከ ተፈቀደልን ዕድሜ እንኖራለን፡፡ በዚህ ሂደት ግን በራስ ፍቃድና አንዳንድ አስቻይ ሁኔታዎች ስም ሊቀየር ይችላል፡፡
እስኪ ስንቶቻችሁ ናችሁ የስማችሁ ትርጉም አግርሞት የፈጠረባችሁ? ወይም ትርጉሙ ለየት ያለ ስም ስትሰሙ የተገረማችሁ? …መልካም ዛሬ ላይ አንድ ሰው ልናስተዋውቃችሁ ነው፡፡
ከደሴ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ወረኢሉ ከተማ ነው የተወለደው፤ ወረኢሉን ስናስብ የአፄ ሚኒሊክ የጣሊያንን ወረራ ለመመከት በጥቅምት ወረኢሉ እንገናኝ በማለት ያስተላልፉትን የክተት ጥሪ እናስታውሳለን፡፡
የወረኢሉ የክተት ጥሪ የጥቁሮቸ ድል የሆነው የአድዋ ድል ጥንስስ ነው፡፡ ታዲያ በዚህች ከተማ 1983 ዓ.ም በእነ መምህር ዓባይ ቤት በተሰማው የዕልልታ ድምፅ ወንድ ልጅ የቤተሰቡ አዲስ አባል ሆኖ ተቀላቀለ፡፡ መምህር ዓባይ በወረኢሉ ከተማ ታዋቂ የህብረተሰብ ሳይንስ መምህር ናቸው፡፡ ክፍል ውስጥ ገብተው ሲያስተምሩ ሁሌም ስለ አባይ ወንዝ ሲያሰቡ ውስጣቸው ይንገበገባል፡፡
ሃገራቸው ከዚህ ታላቅ ወንዝ መጠቀም አለመቻሏ የእግር እሳት ይሆንባቸዋል፤ ይህ የመምህር ዓባይ ቁጭት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ መምህር ዓባይ ቤተሰቡን ለተቀላቀለው ወንድ ልጃቸው ስም ለማውጣት አልተቸገሩም፡፡ ሁሌም አእምሯቸው ውስጥ የኖረና የተሰናዳ ስም ነው፤ ልጄን ይገደብ ብየዋለሁ አሉ፡፡ ብላቴናው ገና ከአራስ ቤት ጀምሮ ስሙ ይገደብ ሆኖ ፀና፡፡
ይገደብ ዓባይ አሁን ላይ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን፣ ያለችውን የስራ ሰአት አጣቦ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ ይገደብ ሰው ተግባቢና ተጫዋች ነው፡፡ ስለ ስም አወጣጡና የነበሩ ገጠመኞችን አውግቶናል፡፡ ስሙን ወላጅ አባቱ እንዳወጡለት እና በልጅነት ጊዜ የስሙ ትርጓሜ ከመጠሪያነት ያለፈ እንዳልነበር ነው የነገረን፡፡
ይገደብ፡- እንደ እኩዮቹ ሰፈር ሲጫወት እና የትምህርት ቤት ህይወት ሲጀምር ስሙ ናኘ፤ ይገደብ የሚለውን ነጥሎ የሚጠራ ጠፋ በሙሉ ስሙ ይገደብ ዓባይ፡፡ መሄድ ካሰበበት ቦታ ሁሉ ቀድሞ ስሙ ይደርሳል፤ ለዚህም እንደምሳሌ በወቅቱ እሱ ሳይገኝ የትምህርት ምዝገባ እንደተከናወነለት ጭምር ነግሮናል፡፡ የሰፈር እኩዮች፣ የትምህርት ቤት ጓደኞች እና ማህበረሰቡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ስሙ ትርጓሜ ግዙፍነት እየነገሩት ነው ያደገው፡፡
በተለይ መምህራን እና ሌሎች የስሙን ትርጓሜ የተረዱ ስዎች በቀልድ እያደረጉ ግብፆች እንዳይሰሙህ ይሉት እንደነበር የሚገልጸው ይገደብ፣ ይሁን እንጂ ለምን እንደዛ እንደሚሉት ግን ነብስ ካወቀ በኋላ እንደረተዳ ነው የተናገረው፡፡ አባቴ ይህንን ስም ሲያወጣልኝ ስሜቱ ወንዙ የተገደበ ያህል ነበር፤ ምክንያቱም ወንዙን ለመገደብ ያኔ የነበረው ዓቅም ለልጁ ስም በማውጣት ነበር በማለት ይገልፃል፡፡
ከትውልድ ቀየው ወረኢሉ በትምህርት እና በቤተሰብ ሁኔታ ደሴ ከዛም ወደ አዲስ አበባ የመጣው ይገደብ፣ ስሙ በተለይ የገነነበትን ጊዜ እንዲህ ሲል ያስታውሳል፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፣ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ የህዳሴ ግድብን ግንባታ የማብሰሪያ የመሰረት ዲንጋይ ሲያስቀምጡ በእነ ይገደብ ቤትም ድርብ ደስታ ሆነ፡፡
ምክንያቱም አባቴ ያቅሙን በልጁ ስም መጠሪያ በማድረግ ምኞቱን የገለፀው የዓባይ ወንዝ ግድብ ሊገነባ መሰረት ድንጋይ ተቀመጠ፤ ይህም ልዩ ክስተት የፈጠረው ስሜት ወደር አልነበረውም ይላል፡፡ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በዜጎች ዘንድ የሚደረገው ድጋፍ ሲጧጧፍ፣ የይገደብ ዓባይ ስምም አብሮ መናኘት እና መግነን ጀመረ፡፡
የ12ኛ ክፍል ትምህርት ማጠናቀቂያ ተመሳሳይ ልብስ ለማሰፋት ወደ ልብስ ስፌት ከጓደኞቹ ጋር ያመራው ይገደብ፣ ስሙን ሲነግራቸው ማመን ያቃታቸው ልብስ ሰፊ፣ መታወቂያ እንዲያመጣ አድረገው ስሙን አይተው በመገረም እንዳስተናገዱት ነግሮናል፡፡ ባንክ አገልገሎት ለማግኘት በተሰለፈበት ወቅት ስሙ ሲጠራ ሰልፈኛው ሁሉ በአግርሞት እና በአድናቆት ድጋፋቸውን ይገልፁለት እንደነበር አጫውቶናል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን ይላል ይገደብ፣ የስሜ ገናናነትን የተረዳሁት ለዩኒቨርስቲ ትምህርት መቐለ ዩኒቨርስቲ በደረስኩ ጊዜ የተደረገልኝን አቀባበል አልረሳውም ይላል፡፡ የወቅቱ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ያደረጉለትን የእንኳን ደህና መጣህ አቀባበል እንዲሁም መቐለ ከተማ ሲገባ የተለየያ ማህበራዊ ሚዲያዎች እና የዜና አውታሮች ይገደብ አባይ መቐለ ዩኒቨርስቲ ገባ፤ እንዲሁም ይገደብ አባይ የሚባል ወጣት ተገኘ የሚሉና ሌሎችም ዜናዎች ከግድቡ ጋር ተያይዘው ይሰሩ እንደነበር፤ ይህም ትልቅ ኩራት እንዲሰማኝ አድርጎኛል ብሎናል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ደስተኛ ያደረገው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን በአካል እንዳገኛቸውና ስሙን ጠርተው እንግዲህ ጀምረነዋል አብረን እንጨርሰዋለን እንዳሉት የነገረን ይገደብ፣ ስራዎች በትውልድ ቅብብሎሽ የሚከወኑ ናቸው፤ እሳቸው ከህዝብ ጋር የጀመሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለፍፃሜ አብቅተውት፣ ለምረቃ መድረሱ ሳስብ ልዩ ስሜት ይፈጥርብኛል ሲል አጫውቶናል፡፡
ስሜ የያዘው ትርጉም ትልቅ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ቢሆንም ግን ከስሜ ባለፈ ለግድቡ ግንባታም ቦንድ በመግዛት ተሳትፊያለሁ የሚለው ይገደብ፣ ከልጅነቴ ጀምሮ ጋዜጠኛ እንደምሆን እያሰብኩ ነው ያደግኩት እናም ቤተሰቤ በግድቡ ሄጄ በሞያየ እንድዘግብ ምኞታቸው ነበር ብሏል፡፡
ይሁን እንጂ እኔ የስፖርት ጋዜጠኛ በመሆኔ፣ ይህ ዕድል አጋጥሞኝ አያውቅም፣ አሁን ላይ ግን ለምረቃው ዕለት የፈጣሪ ፍቃድ ቢሆንና የሚመለከታቸው አካላት ዕድሉን ቢሰጡኝ በቦታው መገኘት ምኞቴ ነው ሲል አጫውቶናል፡፡
ግድቡ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ከስም መጠሪያነት በላይ ነው የሚለው ይገደብ ዓባይ፣ አሁን ላይ ለምረቃ እየተቃረበ መሆኑን ለውስጤ ስነግረው ያሳደግከው ልጅ ለወግ ለማዕረግ እንደ ማድረስ ነውና ከወዲሁ ለምረቃ ዕለት የምለብሰውን ሁሉ እያሰብኩ ነው ሲል ሃሳቡን አካፍሎናል፡፡
በያለው ጌታነህ
AMN – ነሐሴ 16 /2017 ዓ.ም