የሴቶችን ስብራት የጠገነው – ለነገዋ

You are currently viewing የሴቶችን ስብራት የጠገነው – ለነገዋ

‎AMN- ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም

‎ስለ ሴቶች ይወራ ይነገር ቢባል ብዙ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ እሰኪ ጥቂቶቹን እናንሳ፡- “ከጠንካራ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች፤ ሴቶች የዓለም ማጣፈጫ ቅመሞች ናቸው” ሌሎችንም ማለት እንችላለን፡፡

በስነ-ፅሁፍ እና በሌሎች አውዶች ስለ ሴቶች ብዙ ቢባልም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን በማህበራዊ ህግ እና አኗኗር በሚከሰቱ ችግሮች እና ቀውሶች ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሾች ናቸው፡፡ ታዲያ ይህንን መቀየር የትውልዱ የቤት ስራ ነው፤ ትላንት ዛሬ አይደለምና፡: ለሴቶች ምሳሌ የምትሆን ትላንት ሰማይ ምድሩ ጨልሞባት ተስፋ ቆርጣ ሞትን ፀጋ አድርጋ የተቀበለች፣ ነገር ግን ለሞት የተጎነጨችው ፅዋ ከመግደል ይልቅ አዲስ የመኖር ዕድል ከፈተላት፡፡

አሁን ላይ የዓለማችን አብሪ ኮከብና የሴቶች ምሳሌ ተደርጋ የሚትወሰደው ኦፕራ ዌንፍሪ፣ ዛሬ ላይ ለመድረሷ ነገሮች ሁሉ አልጋ ባልጋ ሆነውላት አልነበረም፡: በቅርብ ሰዎቿ ጭምር የመደፈር አደጋ ገጥሟት ህይወት በጨለመባት ጊዜ አጠገቧ ችግሯን ችግሬ ብሎ ከጎኗ የቆመ አልነበረም፡፡ ቢሆንም ግን በፅናት መከራዎችን ሁሉ አልፋ ዛሬ ከፍ ብላ አንደትታይ አድርጓታል፡፡

ታዲያ በዓለማችን ብሎም በሀገራችን በአመራር ሰጭነት፣ በስራ ፈጠራና የሙያ ብቃት አርአያ የሆኑ እንስቶች ቁጥር ለውጥ አለው ቢባልም ዛሬም ላይ የሴቶች ማህበራዊ ችግር ተጋላጭነት የአደባባይ ሚስጥር ነው ፡፡ ሴት ልጅ፣ እናት፣ ሚስት፣ እህት፣ ልጅ ብትሆንም በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የሚገጥሟት የህይወት ፈተናዋም በዚያው ልክ ነው።

‎ችግሮቹን ማንሳትና ለችግር ተጋላጭ መሆናቸውን ማንሳት ችግሩን የባለቤትነት ስሜት ያሳጣል፤ የሩቅ ተመልካች ያደርጋል፤ እንጂ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ታዲያ ችግሩን የራስ አድርጎ በማሰብ ”የማህበረሰቡ አንድ አካልና አምሳል የሆኑት ሴቶች እድል እንጂ ችሎታ አላጡም” የሚለው መሪ ሀሳብ እውን ለማደረግ በተለያየ አጋጣሚ ስራዎች አልተሰሩም ባይባልም በርካቶቹ ግን ከመፈክር ያለፉ አልነበሩም፡፡

ይህንን የተረዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጥልቅ ጥናት መነሻ በማድረግ በከተማዋ የሚስተዋሉ የሴቶችን ማህበራዊ ችግሮችን በዘላቂነት የሚፈታ ለነገዋ የሴቶች ተሀድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከልን እውን አድርጓል፡፡

ማዕከሉ ሴቶችን በስነ-ልቦና በዕውቀት እና በክህሎት ራሳቸውን የሚያበቁበት፣ ከዛም ወደ ስራ ዓለም ተቀላቅለው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡበት ዓቅም እንዲፈጥሩ በተሰራው ስራ በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ይህ ማዕከል በመከፈቱ በጆሮ ለመስማት የሚከብድ ቅስም ሰባሪ የህይወት መሰናክል ውስጥ የነበሩ ሴቶችን ከጎዳና ህይወት በመታደግ እንደ ውሃ ዳር ቄጤማ ተስፋቸውን አለምልሟል። ኤ ኤም ኤን ዲጂታል በማዕከሉ በመገኘት በስልጠና ላይ ካሉ እንስቶች ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ የተካተቱ እንስቶች ስም ለሴቶቹ ማህበራዊ ተጋላጭነትን ለመላከል ሲባል ስማቸው በመቀየር የተዘጋጀ ነው ፡፡

ህይወት አየለ ትባላለች ከ18 ዓመታት የጎዳና ህይወት በኋላ አዲስ የመኖር ተስፋ እንዲኖራት የሚያደርግ ህልምም ሃሳብ ይኖራል ብላ አስባ አታውቅም፡፡ ቀናት እና ወራት መሽተው ከመንጋት ስማቸውን እየቀያየሩ ከመፈራረቅ ውጭ ጠብ የሚል ተስፋ አልነበራትም፡፡ የለነገዋ ማዕከልን ላሰቡና ለጠነሰሱ ወደ ተግባር ላስገቡ የሃሳብ ባለቤቶች ምስጋና ይሁንና ራሷን በዚህ ማዕከል ስታገኝ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ነበር የተሰማት፡፡

በስምንት ዓመታት የጎዳና ላይ ህይወት ያሳለፈችውን ችግር እና መከራ የተጋፈጠችውን የህይወት ጋሪጣ፣ ስታስበው ዕንባ ይቀድማታል፡፡ ያለፈውን ከማሰብ ነገን ተስፋ ማድረጉ ነገሮችን እንድረሳና አዲስ ምዕራፍ እንድጀምር ብርታት ይሰማኛል ትላለች፡፡ ህይወት፣ ጎዳና ላይ አስከፊ ኑሮ ብትገፋም ተፈጥሮ ያደላት የተስተካከለ ቁመናና ሙሉ ጤንነት ባለቤት ነች፡፡ ይህም በማዕከሉ ያገኘችውን ዕድል በትጋት እንድትፈፅም አግዟታል፡፡

‎ህይወት፣ አሁን ላይ በማዕከሉ ያላትን ቆይታ እንዲህ አጫውታናለች፡፡ “የልጅነት ህይወት ናፍቆኝ ነበር አሁን እያጣጣምኩት ነው፤ ርካሽ የሆንኩ መስሎኝ ነበር አሁን ውድ ሰው ሆኛለሁ” ስትልም ትገልፃለች፡፡ የተማርኩት የምግብ ዝግጅት ነው የምትለው ህይወት፣ አባቴ በህይወት እያለ ወጥ ቤት ተቀጥሮ ይሰራ ነበር፤ ስትል ታስታወሳለች፡፡ ለሞያውም ፍቅር ያደረባት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደነበር በማንሳት።

በምግብ ዝግጅት አባቴን አይበታለሁ፤ ሰርቼም እለወጣለሁ፤ በጎዳና የወለድኩትን ልጄን በእናት ፍቅር ማሳደግ የሚያስችል ተስፋ አግኝቻለሁ” ስትልም ሳግ እየተናነቃት ነው ያጫወተችን። የአፍላ ዕድሚያችን እና ጊዚያዊ ደስታ ሳያዘናጋን ነጋችንን እንኑር የምትለው ባለተስፋዋ ህይወት አየለ፣ የለነገዋ ሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል የዓለም ምሳሌ ነው ስትል ነው የገለፀችው።

‌‎ሌላኛዋ የማዕከሉ ተጠቃሚ ዓለም ዘመነ፣ እንቅልፍ ማጣትን ርሃብና ጥምን እየመረረን ኖረንበታል ትላለች፡፡ ታዲያ ዛሬ ላይ ትላንትን በነበር አሳልፌ በወሰድኩት ስልጠና ተመርቄ ወደ ስራ ለመቀላቀል የምረቃ ቀኔን በጉጉት እየጠበቅኩ ነው ስትል ተስፋዋን አጋርታናለች ፡፡

ሃዊ አለማየሁ ከዚህ ቀደም በማዕከሉ ከነበሩ ሰልጣኞች አንዷ ነች፡፡ ሃዊ የአካል ጉዳተኛና የስነ-ልቦና ችግር ተጠቂ እንደነበረች ገልፃ፣ ከዚህ አስከፊ ህይወት እንድትወጣ ዕድሉን በዚህ ማዕከል በማግኘቷ በማዕከሉ ውስጥ የስራ እድል ተመቻችቶላት በቤተ-መጽሐፍት ባለሙያነት እየሰራች እንደምትገኝም ገልፃለች።

በዚህ ማዕከል ውስጥ‎ እንደ ህይወት አየለ እና ሌሎች ሰልጣኞች የትላንት አስከፊ የህይወት ገመናቸውን ወደ ኋላ ትተው፣ ነገን ተስፋ የሰነቁ የመኖርን ትርጉም እንዲረዱ ዕድል ያገኙ እንስቶች፣ ትላንትን ታሪክ ሊያደርጉ በማዕከሉ ተሰባስበዋል፡፡ እንደየ ዝንባሌያቸው፣ የትምህርት ደረጃቸው እና ምርጫቸው ስልጠናዎችንም እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ አሁን ላይ ለእነዚህ እንስቶች በምድር ከዚህ የተሻለ ገነት የለም፡፡ ምክኒያቱም የትላንት ችግርና መከራቸውን ከላያቸው አራግፈው የነገ አዲስ ተስፋ መንገዳቸውን እየጠረጉ ነው ፡፡

‎ለነገዋ ሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል የጤና ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሲስተር ልኬ ኃይለማርያም በበኩላቸው፣ በማዕከሉ የተሟላ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አንስተው፣ በመጀመሪያ ዙርና ሁለተኛ ዙር 682 ሴቶች ሰልጥነው ስራ ላይ መሰማራታቸውን አመልክተዋል። በሰልጣኞቹ ዘንድ ከአንደበታቸው አንድ ነገር አይለይም፤ ይህም የከተማ አስተዳደሩን ከፍተኛ አመራሮች እና የማዕከሉ አጠቃላይ ሰራተኞች ምስጋና፡: በማዕከሉ የሚገቡ ሴቶች ከሱስ እንዲያገግሙ በማድረግ በቂ ስልጠና እና የስነ-ልቦና ድጋፍ ካገኙ በኋላ እችላለሁ የሚል መንፈስ አዳብረዋል ሲሉ ተናግረዋል። ‎ተቋሙ በ2030 የሴቶች ልህቀት ማዕከል ለመሆን ራዕይ ሰንቆ ከወዲሁ ራዕዩን ለማሳካት ውጤታማ ስራ አየሰራ ይገኛል ።

‎በአለኸኝ አዘነ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review