በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ በጎርፍ ጉዳት ደርሶበት የነበረው የጌደብ ወንዝ ድልድይ በተገጣጣሚ ብረት ድልድይ እንደገና ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን የዞኑ መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ ማናየ አዳነ እንደገለጹት፣ ድልድዩ በጎርፍ ምክንያት ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የደብረ ማርቆስ መንገድ ጥገና ዲስትሪክት ጋር በመተባበር በተገጣጣሚ ብረት መልሶ ለመገንባት ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል።
በዚህም የተገጣጣሚ ድልድዩ ግንባታ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ትናንት ምሽት ለእግረኞች ክፍት መደረጉን አስታውቀዋል።
ለተሽከርካሪዎች ደግሞ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ክፍት እንደሚደረግ የመምሪያ ኃላፊው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ድልድዩ በጎርፍ ምክንያት ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ሲጠባበቁ ለቆዩ መንገደኞችና አሽከርካሪዎች ላሳዩት ትዕግስት ምስጋና አቅርበዋል።
የጌደብ ወንዝ ድልድይ ነሐሴ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በጮቄ ተራራ ላይ የጣለው ዝናብ በፈጠረው ከፍተኛ ጎርፍ በደረሰበት ጉዳት፣ ከደብረ ማርቆስ ወደ ባህርዳርና ሌሎች ወረዳዎች የሚደረገው የትራንስፖርት አገልግሎት ተስተጓጉሎ መቆየቱን አውስተዋል።