“የኮሪደር ልማቱ ለአፍሪካምሳሌ ሆኗል”

You are currently viewing “የኮሪደር ልማቱ ለአፍሪካምሳሌ ሆኗል”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
• አዲስ አበባን የማስዋብ ስራ በተገባው ቃል መሰረት መፈጸሙን ገልጸዋል

“ከተሜነት የሰው ልጅ የብልጽግና መዳረሻ ነው፡፡” ይህን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግሥት በተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው ዙሪያ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የመደመር መንግስት ለከተማና ከተሜነት ባለው መረዳት መሰረት ከተሜነት የሰው ልጅ የብልጽግና መዳረሻ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ለነዋሪው ምቹ ከተማን በመፍጠር ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከተማ እና ከተሜነት ለሀገር ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ድርሻ ስለሚይዝ የመደመር መንግስት የላቀ ትኩረት እንደሚሰጠውም  አብራርተዋል። የከተሞችን እድገት በማጣጣል ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደማይቻል ጠቁመው፣ የመደመር መንግስት ለገጠሩም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል፡፡ በኮሪደር ልማት በርካታ ዜጎች የስራ እድል ከማግኘታቸውም በላይ ለዝርፊያ እና ለተለያዩ ወንጀሎች ተጋላጭ የነበሩ ወገኖች ደህንነታቸው መረጋገጡን  ገልፀዋል፡፡

በርግጥም “የከተሞችን እድገት በማጣጣል ብልጽግናን ማረጋገጥ አይቻልም” የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀሳብ ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ አያሌ መረጃዎችን እና የሀገራትን ተሞክሮ መጥቀስ እንችላለን፡፡

ለዚህ ደግሞ በከተሞች ኢኮኖሚና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥናታዊ ጽሑፎችን እና መፅሐፍትን ያሳተሙት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ግላይዘር እ.ኤ.አ በጥር 31 ቀን 2012 “የከተሞች እውነት ወይም ድል” (Triumph of the City) የተሰኘው ጥናታዊ መፅሐፋቸው አንዱ ምስክር ነው፡፡

ፕሮፌሰር ኤድዋርድ በመፅሐፋቸው እንዲህ ይላሉ፤ ከተሞች የሀገራት ልብ ምት፣ የስልጣኔ መግቢያ በር፣ የምጣኔ ሀብት ርካብ፣ ቀን ነፍስና ስጋን ማስደሰቻ፤ ማታ ደግሞ ጨለማውን መርቻ የድል መቅረዝ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰሩ በመፅሐፋቸው የከተማ ኑሮ መሻሻል፣ ምርታማነትን፣ ባህልን እና የሰው ልጆችን ደስታ ከፍ በማድረግ ለሀገራት ሁለንተናዊ ከፍታ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አሁን በተምሳሌትነት የምንጠቅሳቸው የዓለም ሀገራት የዕድገታቸው ምስጢር የከተሞቻቸው ከፍታ እንደሆነ በተጨባጭ መረጃዎች እያጣቀሱ ገልፀዋል፡፡

ከተሜ መሆን ማለት ወደ ብልፅግና መቀራረብ ማለት መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህም የሰው ልጆች ኑሮን ምቹ የሚያደርግ አገልግሎትን የሚያቀልል እና ነገሮች በተሻለ መንገድ የሚቀርቡበት ኑሮ ከተሜነት ነው፡፡ ለአብነትም ህክምና፣ ትምህርት እና ትራንስፖርትን ለማግኘት ቀላል፤ ብዙ  ነገሮችም የዘመኑና ቀለል ያሉ ናቸው፡፡ ይህም የከተሜነት መገለጫ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ከተማና ከተሜነትን ይበልጥ ለመገንዘብ በአራት መነፅሮች እንመልከታቸው ያሉት ጠቅላይ  ሚኒስትሩ፣ የመጀመሪያው በማህበራዊ  እይታ ነው፡፡ ይሄውም ከተሞች ቅይጥ  ባህል መፈጠሪያ ማዕከላት ናቸው፡፡ በአንድ ከተማ ውስጥ ከዚህም ከዚያም ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት … ያለው ሰው ስለሚመጣ የቅይጥ ባህል መፍጠሪያ ማዕከል አድርገን የምንወስደው ከተሞችን ነው፡፡

ከተሜነት ደግሞ ስርዓት ያለው ህብር መፍጠሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ለአብነትም በትራንስፖርት፣ በቆሻሻ አወጋገድ፣ በአገልግሎት እና በልዩ ልዩ ነገሮች ስርዓት ባለው መንገድ በአንድነት እንዲፈስሱ የማድረግ ማህበራዊ አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛው መነፅር ኢኮኖሚ ነው። ለአብነትም ከተሞች ለንግድ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለስራ ፈጠራ እና ለቴክኖሎጂ ቅርብ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የዓለማችን ከተሞች ያላቸው ሀብት ከአጠቃላይ የሀገር ሀብት ጋር ሲነፃፀር ለውድድር የሚበቃ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለአብነትም አዲስ አበባን ጠቅሰዋል፡፡

አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀብት አምሳ በመቶውን ትይዛለች፡፡ ለዚህ  ደግሞ ብዙ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ፈጠራ ያለባት ከተማ መሆኗን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡ በመሆኑም ከተሜነት የላቀ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው ብለዋል፡፡

እድገትን የምናስብ ከሆነ ከተሞች ላይ ኢንዱስትሪን እና  ፈጠራን  ማስፋት አለብን፡፡ ምክንያቱም ኢንዱስትሪ ሰው ይፈልጋል፡፡ ሰው የምንቀጥር ከሆነ ደግሞ መኖሪያ ቤት ይፈልጋል፡፡ መኖሪያ ቤት ካለ በቂ ውሃ፣ መብራት፣ ጤና፣ ለልጆች  ትምህርት ቤት  እና መሰል አገልግሎቶችን እና መሰረተ ልማቶችን ይፈልጋል፡፡

ሦስተኛው መነፅር ፖለቲካ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከተሞች የዳበረ የፖለቲካ ስርአት  መፍለቂያ ማዕከላት ናቸው፡፡ የፖለቲካ ስርአት ዳብሮና በስሎ ለሀገር በሚበጅበት መንገድ  የሚታይበት አንዱ  አውድ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ከተሜነት ደግሞ  ስልጣኔ፣ ውይይት እና ንግግር መፍትሔ ማምጫ  ማዕከል ነው፡፡

አራተኛው መነፅር  አካባቢያዊ ዕይታ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከተማ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ  ስርዓት ጋር ውስብስብ ስነ ምህዳር ውስጥ የሚኖርበት ነው፡፡ ለምሳሌ በገጠር ቆሻሻን ማስወገድ እንደ ከተማ ስርዓት ያለው ማስወገጃ ላይፈልግ ይችላል፡፡ በከተሞች ግን ከእያንዳንዳችን ቤት የሚወጣው ነገር በተንሰላሰለ መንገድ መጓዝ አለበት፡፡ በመሆኑም ከተፈጥሮ ስርዓቶች ጋር ውስብስብ ስነ ምህዳር መፍጠር ካልተቻለ ይበላሻል፡፡

ስለዚህ ከተሜነት የውበት፣ የጤናማነት እና የዘመናዊ አኗኗር ዘዬ መገለጫ መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከተማን በመተው፣ በማናናቅ፣ በማራከስ የሆነ ስፍራ እሰራለሁ ብሎ በተናጠል ማሰብ ብልፅግናን እንደማያረጋግጥ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ ለማድረግ በታቀደው መሰረት ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአብነትም የሰው ልጆችን ኑሮ ምቹ ማድረግ፣ አገልግሎትን ማቅለል፣ ነገሮችን በተሻለ መንገድ ማቅረብና ማሟላት መሆኑን በመገንዘብ የከተሜነትን የኑሮ ዘዬ ለማስፋፋት እየተሰራ ነው፡፡ በዚህም ውጤት ተገኝቷል፡፡ አዲስ አበባን የማስዋብ ስራ ቃል ገብተን ፈፅመናል፡፡ ብልፅግና ከተማን ብቻ እያለማ ገጠርን የሚተው አይደለም በሁለቱም ጥሩ እና ውጤታማ ስራ እየሰራን  እንገኛለን ብለዋል፡፡

ለዚህም በቅረቡ የሚመረቀው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት የሚያስደምም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአርሶ አደሩን ህይወት በብዙ የሚያዘምንና የሚያሻሽል ነው ይህም መንግስት ገጠርንም ያካተተ ዘላቂነት ያለው ስራ እያከናወነ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር እና የወንዞች ዳርቻ ልማት በምናባዊ እይታ በብዙ መትጋት የመጣ ለውጥ፣ በተለያየ መልኩ ለአፍሪካውያን ከተሞች ተምሳሌት የሆነ እና  ሀገርን የሚያኮራ ስራዎች የተሰሩበት እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጀማ ሀጂ እንደሚሉት በአዲስ አበባ ተጀምሮ ወደ ሌሎች ከተሞች በመስፋፋት አስደናቂ የከተሞች ለውጥን እያሳየ ያለው ኮሪደር ልማት በከተሞች መካከል የትብብር መንፈስን ያበረታታል፤ ለተሻለ የኑሮ ሁኔታ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ለዘላቂ እምርታ ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው፡፡ እንዲህ አይነት ልማት በተለይም አሁን ያለው ብቻ ሳይሆን መጭው ትውልድ በተጎሳቆለ አካባቢና ሁኔታ ውስጥ ሕይወቱን በአስቸጋሪ መልክ እንዳይገፋና ደስተኛ ሆኖ የሀገሩን ከፍታ እንዲያስቀጥል ትልቅ አበርክቶ አለው፡፡ ዓለም አቀፍ እውነታውም የሚያሳየው ይህንኑ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ጀማ ሀጂ በገለፃቸው፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በኮሪደር እና በወንዞች ዳርቻ ልማት ከተሞችን ማስዋብ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ምቹ ማድረግና አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎችን የመገንባት ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ይህንን ስራ እያዩ እንደ ሰው በተቃራኒው መቆም አይቻልም። ለአብነትም አዲስ አበባ ተለውጣለች፤ ይህንንም ዐይተን እየመሰከርን ነው ብለዋል፡፡

በከተማዋ እየመጣ ያለው ለውጥም “ለካ በሀገራችን እንዲህ አይነት ነገር መስራት ይቻላል? እኛም ማድረግ እንችላለን?” የሚል ስሜትን የሚፈጥር ነው፡፡ እነዚህ ተግባራት የከተማዋን ኢኮኖሚ በማነቃቃት እንደ ሀገር የሚኖራቸው ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም በዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ላይ የተመሰረተ ሆኖ እንዲቀጥል ሁሉም ዜጋ ይህንን ልማት በተለያዩ መንገዶች ማገዝ ይኖርበታል ሲሉ አክለዋል፡፡

በርግጥም ከተማዋን ከስልጡን የዓለማችን ከተሞች ተርታ ለማሰለፍ እየተሰሩ ባሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች አዲስ አበባ በትክክልም አዲስም፣ አበባም እየሆነች መምጣቷን በተከታታይ እየተከናወኑ ያሉ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ታላላቅ ጉባኤዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በሌላ በኩልም ከቦሌ እስከ መገናኛ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ፒያሳ፣ ከፒያሳም በቸርችር ጎዳና ወደ ሜክሲኮ፣ ከስድስት ኪሎም እስከ እንጦጦ. . .  ቢያሻን በመኪና ቢለንም በእግር ዘወር ዘወር ብንል ልማቱ እራሱ ይናገራል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review