ማንኛውም የሕዝብ አገልጋይ

You are currently viewing ማንኛውም የሕዝብ አገልጋይ

”ሀገሬ ይህን ካደረገችልኝ፤ እኔ ደግሞ የምችለውን ሁሉ ላድርግላት’ በሚል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል”

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር)

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለመንግስት ሠራተኛው ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ መንግስት መወሰኑን አሳውቋል፡፡ በመግለጫው ላይ እንደተጠቆመው፤ ይህ የደመወዝ ማሻሻያ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን በመሠረታዊነት ለመፍታት ሀገራችን እየተገበረቻቸው ባሉ ማሻሻያዎች የተያዙ ሁለት ዓላማዎች አካል በመሆኑ ነው፡፡  እነዚህ ሁለት ዓላማዎች ተብለው የተጠቀሱት፤ ነባር ሀገራዊ ስብራቶችን መጠገንና የተንከባለሉ ዕዳዎችን ማቃለል እንዲሁም የዛሬንና የነገን ትውልድ ጥያቄዎች በመመለስ የኢትዮጵያን ብልጽግና በአስተማማኝ መሠረት ላይ መገንባት የሚሉ ናቸው፡፡ የደመወዝ ጭማሪውም ከሁለተኛው ዓላማ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ከመስከረም ወር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለሚፈፀም የመንግስት ሠራተኛ ደመወዝ ማሻሻያ ወጪ  ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ጠይቋል፡፡ ይሄም እንደ ሀገር ለመንግስት ሠራተኛው ለደመወዝ የሚወጣውን ጠቅላላ ዓመታዊ የመንግሥት ወጪ 560 ቢሊዮን ብር ያደርሰዋል።

ከፍተኛ በጀት ወጪ የተደረገበት የመንግስት ሠራተኛ ደመወዝ ማሻሻያ በውጤታማነት ተፈፃሚ እንዲሆን፣ በተለይም የደመወዝ ማሻሻያው ተጠቃሚ የሆነው በመንግስት ተቋማት መዋቅር ውስጥ ያለው የሠው ኃይል በተሰማራበት መስክ ምርታማነቱ እንዲጨምር እና የሚሰጠው አገልግሎት እንዲሻሻል በማድረግ ረገድ መከናወን ስላለበት ስራ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡

የደመወዝ ማሻሻያውን በበጎ እርምጃ እንደሚመለከቱት የጠቆሙት ሞላ (ዶ/ር)፤ “የገንዘብ የመግዛት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሄድ ተፈጥሯዊ ነው። በዚህ ዑደት ውስጥ በአብዛኛው ተጎጂ የሚሆኑት በቋሚ ወርሃዊ ደመወዝ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ናቸው፡፡ በተለይ የገንዘብ የመግዛት አቅም ፈጣን በሆነ ለውጥ ውስጥ ሲሆን፤ በማይለዋወጥ ደመወዝ የሚሠሩና ኑሯቸውን በደመወዝ ገቢ የሚመሩ ሠዎች ተጎጂ ይሆናሉ። መንግስትም ከመስከረም ወር 2018 ዓ.ም. ለሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ ለማድረግ መወሰኑ የሚደገፍ እርምጃ ነው፡፡ ይህም በኑሮ ጫና እየተፈተኑ የሚገኙት የመንግስት ሠራተኞች ቢያንስ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ያለመጨናነቅ ማሟላት የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል” ሲሉ አንስተዋል፡፡

ከፍተኛ ተመራማሪው እንዳብራሩት፤ የአንድን ሀገር ልማትና ብልፅግና ከሚያመጡ ወሳኝ አቅሞች መካከል፤ የሠው ኃይል፣ ገንዘብ (ካፒታል) እና መሬት (የተፈጥሮ ሃብት) ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ ሁሉ ደግሞ የሠው ኃይል ቁልፉና ቀዳሚው ነው፡፡ ምክንያቱም ሌሎቹ አቅሞች (ገንዘብ እና መሬት) ካለሠው ምንም ናቸው፡፡ የሠው ኃይል ሲባል ደግሞ፤ የተማረ እና የሠለጠነ መሆን አለበት፡፡ ዕውቀት፣ ሙያዊ ክህሎት እና ልምድ ያለው የሠው ኃይል ከሁሉም የበለጠ አቅም መሆኑን በተግባር ለማረጋገጥ፣ ሥራዎቹን በተነሳሽነት፣ በብቃት እና በአግባቡ መከወን ይኖርበታል፡፡

“እንደሀገር ካለው አቅም አንፃር ለደመወዝ ማሻሻያ የተመደበው ገንዘብ በጣም ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ቀላል ለማይባሉ የመሠረተ ልማት ግንባታ እና ሌሎች ሥራዎች ማከናወኛ ሊውል የሚችል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለሠራተኛ ደመወዝ እንዲውል በመንግስት መወሰኑ፤ የሠው ኃይሉ ዘላቂነት ላለው የሀገር ልማት እና ዕድገት ምን ያክል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው” ያሉት ሞላ (ዶ/ር)፤ “የደመወዝ ማሻሻያ የተደረገለት ማንኛውም የሕዝብ አገልጋይ ‘ሀገሬ ከሌላት ሃብት ላይ ቀንሳ ይህንን ካደረገችልኝ፤ እኔ ደግሞ የምችለውን ሁሉ ላደርግላት ይገባል’ በሚል አስተሳሰብ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በብቃት ሊወጣ ይገባል፡፡ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን ህብረተሰብ እርካታ ማሻሻል ይኖርበታል። ሥራዎችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ አግባብ መከወንን የየዕለት ተግባሩ ማድረግ ይጠበቅበታል” በማለት ምክረ ሃሳባቸውን ለግሰዋል፡፡

አክለውም፤ እንደ ሀገር ምርታማነት እንዲጨምር እና ገቢ እንዲያድግ ሳይታክት መሥራት ከዚህ የሠው ኃይል የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባርና ኃላፊነት መሆኑን አንስተዋል፡፡ ምርታማነት ከጨመረ፣ የሀገር ዕድገት እና ብልፅግና ከተረጋገጠ፣ የደመወዝ ጭማሪ ብቻ ሳይሆን ከዚህም ከፍ ያለ ጠቀሜታን ማግኘት እንደሚችል መገንዘብና የሚጠበቅበትን መወጣት አለበትም ብለዋል፡፡

“የደመወዝ ማሻሻያ ካለን የልማት ፍላጎት አንጻር አገልግሎቶችና መሠረተ ልማት ለማስፋፋት የሚያስፈልገንን ሀብት የሚሻማ ቢሆንም፣ የመንግሥት ሠራተኛውን ኑሮ ማሻሻል ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ የተደረገ ነው” ያለው ነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መግለጫ፤ ከደመወዝ ማሻሻያው ባሻገር የመንግሥት ሠራተኛው ችግር በደመወዝ ማሻሻያ ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ በቀጣይ የቤት አቅርቦትን እና የጤና መድን ሽፋንን ጨምሮ የተለያዩ መፍትሔዎች እንደሚወሰዱ አሳውቋል፡፡

መንግሥት ይሄንን የደመወዝ ማሻሻያ ሲያደርግ ጭማሪው በቂና የመጨረሻ እንዳልሆነ፣  በቀጣይነት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ማሻሻያው እየተተገበረ ሲሄድ ውጤትን መሠረት ያደረጉ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ፣ በተጨማሪም የተጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ይበልጥ ውጤት እያስመዘገበ በሄደ ቁጥር፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የትሩፋቱ ተቋዳሽ እንደሚሆን በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

“የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በተገቢ ደረጃና መጠን ለመክፈል ከተፈለገ፣ ያንን የሚሸከም ሀገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት አለብን” ያለው የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፤ ኢትዮጵያ ለአገልጋዮቿ ተገቢውን ክፍያ እንድትከፍል የሚያስችላትን ኢኮኖሚ የመገንባት ኃላፊነት ደግሞ፣ በመንግሥት ሠራተኛው ላይ ጭምር የተጣለ ብሔራዊ ግዴታ መሆኑን አፅንኦት በመስጠት አመላክቷል፡፡ “ካልተከልነው ዛፍ ፍሬ፣ ካልዘራነው ሰብል ምርት ልናገኝ አንችልም” የሚል ጥልቅ ሃሳብ የያዘ አባባል በመጠቀምም፤ እንደ ሀገር ኢኮኖሚያችን ካላደገ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ሊያድግ እንደማይችል ተገልጿል፡፡ በሀገር ደረጃ የታክስ ገቢን በአንድ በመቶ ማሳደግ ቢቻል፤ ከ300 ቢሊዮን በላይ ተጨማሪ ሀገራዊ ገቢ የሚገኝበት አቅም እንደሚፈጠር በምሳሌ በማሳየት፤ ይሄንን ለማሳካት ደግሞ በየመስኩ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ከፍተኛውን ሚና መጫወት እንደሚገባቸው አሳስቧል፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ከጥቂት ቀናት በፊት፤ የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ወደ ሙሉ ትግበራ ማስገባቱን በማስመልከት በተዘጋጀ መድረክ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ ተሿሚዎችን፣ የጸጥታ አካላትን፣ ዳኞችን ጨምሮ ቁጥራቸው ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ ከፌዴራል ጀምሮ እስከታችኛው አስተዳደራዊ መዋቅር ድረስ ትምህርት ቤቶችንና ጤና ተቋማትን ጨምሮ 1 ሺህ 720 የሚደርሱ ተቋማት አሉ፡፡ የመንግስት ተቋማትን አደረጃጀትና አሰራር በማዘመን በክህሎትና በባህሪ የበቃ የሰው ኃይል አስተዳደርና ልማትን በመዘርጋት ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ሪፎርሞች እየተካሄዱ ናቸው። ከሪፎርሞቹ መካከል የመንግስት ተቋማት አሠራራቸውን በማዘመን ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ፤ የመንግስት ሰራተኛው ስራውን በውጤታማነት በመፈፀም፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ እና አገልግሎት በማሻሻል፣ የሥራ ዲሲፕሊንን በማክበር፣ የሥራ ሰዓትን በአግባቡ በመጠቀም፣ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት ለሀገራዊ ዕድገት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡

የመንግስት ሠራተኛው ይህንን በአግባቡ መፈፀም ከቻለ፤ እንደ ሀገር የተቀመጠው የሪፎርም ዕቅድ ውጤታማ እንደሚሆን ኮሚሽነር መኩሪያ (ዶ/ር) አንስተዋል። የመንግስት ሠራተኛው ተጠቃሚነት በደመወዝ ማሻሻያ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፤ እንደውጤታማነቱ በየጊዜው ማትጊያና ማበረታቻ እየተሰጠው፣ ከዕድገቱና ከልማቱ ተጠቃሚነቱ እየተረጋገጠ፣ መካከለኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ አካል እስከሚሆንበት ደረጃ ድረስ ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በአርሶ አደሩ እና በአርብቶ አደሩም ሆነ በከተማው ነዋሪ ዕድገት ላይ ቁልፍ ሚና ያለው የመንግስት ሠራተኛው የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡና በውጤታማነት ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

“መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያካሄዳቸው ዘርፈ ብዙ ሪፎርሞች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግና ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን አንስተዋል። የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ በተለይም የዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችን ጫና ውስጥ እንዳይከት መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱንም አስታውሰዋል። መንግስት የቋሚ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከመስከረም ጀምሮ የተደረገው ማሻሻያም የዚህ ማሳያ ነው። የመንግስት ሠራተኛውም ሥራዎችን በምርታማነት፣ በወጪ ቆጣቢነት እና በውጤታማነት ማከናወን ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ 

“ለሠራተኞች ደመወዝ ማስተካከያ እንዲሆን የተያዘው ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ ገንዘብ በደመወዝ መልኩ ወጪ ተደርጎ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባ ነው፡፡ በዚህ ላይ በጥናት የተመሠረተ ቀጣይነት ያለው ሥራ ካልተሠራ ገንዘቡ በገበያው ላይ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት አባባሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የዋጋ ግሽበትን ሊያቃልሉ የሚችሉ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን በማቀድ ተፈፃሚ ማድረግ ይገባል” ያሉት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር)፤ ይህን መነሻ በማድረግ በገበያው ላይ የምርት እጥረት በመፍጠር፣ በምርትና አገልግሎቶች ላይ ያልተገባ ጭማሪ በማድረግ እና በመሳሰሉ ምክንያቶች የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላትን ካሉ ከግንዛቤ ፈጠራ ጀምሮ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፣ አለፍ ሲልም አስተማሪ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review