ሆቴሎች እጃቸው ላይ ያለውን እድል እንዴት ሊጠቀሙት ተዘጋጅተዋል?

You are currently viewing ሆቴሎች እጃቸው ላይ ያለውን እድል እንዴት ሊጠቀሙት ተዘጋጅተዋል?

ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት የአየር ንብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

የዓለም አቀፍ ጉባኤዎችና ኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፍ እጅግ ግዙፍና በፍጥነት እያደገ ያለ ኢንዱስትሪ ነው። ይህ ዘርፍ በተለያዩ ጥናቶች ስር ‘MICE’ (Meetings, Incentives, Conferences and Exhibitions) ወይም “የቢዝነስ ዝግጅቶች” በመባል ይታወቃል። ኢቨንት የተሰኘ ገፀ ድር እ.ኤ.አ በ2024 ማይስ ምንድን ነው? (What Is MICE? ) በሚል ርዕስ ባስነበበው መረጃ፣ የዓለም አቀፍ የማይስ ኢንዱስትሪ ገቢ ከ1 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደነበር አስፍሯል። ይህ ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄዶ እስከ 2032 ድረስም ወደ 2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ትንበያው አስቀምጧል።

ይሁንና ዓለም በዚህ ደረጃ ከዘርፉ የሚገባውን እየተቋደሰ ቢሆንም አህጉረ አፍሪካ ግን የሚገባትን ያህል እየሰራችም እየተጠቀመችም አለመሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የዓለም አቀፍ ኮንግረስ እና ኮንቬንሽን ማህበር (ICCA) መረጃም የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ የተቋሙን መረጃ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት አህጉሪቱ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ማህበራት ስብሰባዎች ከገቢ አንጻር ያላት ድርሻ ከ10 በመቶ ያነሰ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ከተለመዱ ውስን ጉባኤዎች በእጥፍ የላቁ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን በስኬት በማስተናገድ ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ ይህንን የአህጉሪቱን መልክ ለመቀየር እየጣሩ ካሉ ከተሞች በቀዳሚነት ትጠቅሳለች፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደሚገልጹትም መዲናዋ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያህል ጎብኚዎች የተሳተፉበትን 150 ዓለም አቀፍ ኩነቶችን በከፍተኛ ስኬት አስተናግዳለች። በዚህም 143 ቢሊዮን ብር ያህል ሀብት ወደ ከተማዋ ኢኮኖሚ ገቢ ሆኗል።

ይህ የገቢ ስሌት ታዲያ ለጉባኤዎቹ ከሚከፈለው ቀጥተኛ ክፍያ በተጨማሪ፣ ተሳታፊዎች በቆይታቸው የሚያወጡት ወጪን ጭምር ሲሆን፣ በተለይም ጉባኤው በሚካሄድበት ከተማ የሚገኙ ሆቴሎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ሆቴሎች፣ ካፌዎች እና ሌሎች ተቋማት የሚያገኙትን ገቢ ያካትታል፡፡ እንደዚሁም ጉባኤውን ተከትሎ ተሳታፊዎች ለግል ግብይትና ለሌሎች መዝናኛዎች የሚያወጡት ገንዘብን ጨምሮ እንደሆነ ልብ ይሏል።

በመጪዎቹ የዻጉሜ እና የመስከረም ወራት ደግሞ መዲናዋ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት፣ 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ 2ኛው የካረቢያን እና አፍሪካ መሪዎች “ካሪኮም” ጉባኤን ታስተናግዳለች፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት የአየር ንብረት ጉባኤ ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የህገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀልን መከላከል ቡድን ዓመታዊ ጉባዔ ደግሞ ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ  ይካሄዳል፡፡ ለመሆኑ እንደዚህ አይነት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማስተናገድ ለመዲናዋ ያለው ትርጉም ምንድነው? በተለይም በመዲናዋ የሚገኙ ሆቴሎች እድሉን ለመጠቀም ምን ያህል ተዘጋጅተዋል? የሚሉና መሰል ጉዳዮችን መፈተሽ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከሆቴል ኢንዱስትሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በቅድመ ዝግጅት ስራዎች ዙሪያ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት እንደገለፁት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለዘርፉ ልማት የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት አመላክተዋል፡፡ የሀገራት መሪዎችን፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ የአየር ንብረት ተመራማሪዎችን፣ ዓለም አቀፍ የሚዲያ አካላትን ጨምሮ ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት የአየር ንብረት ጉባኤ በመዲናዋ መካሄድም መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ስጥቶ የመስራትን ተገቢነት የሚያረጋግጡ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።

አክለውም ለውጤቱ መመዝገብ አዲስ የተገነቡ፣ የታደሱ ነባር የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች የእንግዳ ተቀባይነትና ተባባሪነት፣ የግሉ ዘርፍ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የመንግስት የተናበበ ቅንጅት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸውም እንደዚሁ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አንስተዋል።

ሆቴሎች የቱሪዝም ዘርፍ ዋነኛ አካል ስለመሆናቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ በስቴለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያ ሮኒ ዶናልድሰን እንደሚሉትም ሆቴሎች ለሀገሪቱ ባህልና ቅርስ ትልቅ ማስተዋወቂያ መድረክ ሆነው ያገለግላሉ። ብዙ ሆቴሎች የሀገራቸውን ባህላዊ ምግቦችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ የሀገርን ማንነት ለውጭ ጎብኚዎች ያስተዋውቃሉ። ይህም የባህል ቅርሶች እንዲጠበቁና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ይረዳል፤ በዚህም የሀገርን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስ የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ ይደገፋል።

ከዚህ አንጻር ሲመዘን በቅርቡ በአዲስ አበባ የሚከናወነው የአየር ንብረት ጉባኤ በከተማዋ ለሚገኙ ሆቴሎች በአንድ በኩል ትልቅ ኃላፊነት የሚሰጥ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር እሙን ነው፡፡ ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች በአንድ ጊዜ ወደ ከተማዋ ሲመጡ ለመኝታ፣ ለመመገቢያ እና ለሌሎች አገልግሎቶች ያለው ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል። የጉባኤው ተሳታፊዎች በቆይታቸው ሆቴሎች ሙሉ በሙሉ የመያዝ ዕድል አላቸው። ይህም ከኪራይ ገቢ በተጨማሪ በምግብና በመጠጥ አገልግሎቶችም የላቀ ጥቅም ያስገኛል። ከዚህም ባሻገር፣ ጉባኤው ከተማዋን እንደ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እና ኤግዚቢሽኖች (MICE) መዳረሻነት እንድትታይ ያደርጋታል። ይህም በቀጣይነት ሌሎች ተመሳሳይ ትላልቅ ጉባኤዎችን ለመሳብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

አዲስ አበባ ከዚህ በፊትም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችንና የዩኒየን ጉባኤዎችን በተደጋጋሚ አስተናግዳለች። ከእነዚህ ልምዶች መረዳት እንደሚቻለው በጉባኤ ወቅት የሚስተናገዱ እንግዶች ለሆቴሎች የገንዘብ ፍሰት ከመፍጠራቸው በተጨማሪ፣ ዘላቂ የንግድ ግንኙነቶች እንዲመሰረቱ ያግዛሉ። በርካታ ሆቴሎች በጉባኤው ላይ ከሚሳተፉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ለወደፊትም እንግዶችን የማግኘት ዕድላቸውን ያሰፋሉ። በተጨማሪም ትልልቅ ዝግጅቶችን ለማስተናገድ የሚያስፈልገው ዝግጅት የሆቴሎችን የአገልግሎት ደረጃ የሰራተኞችን አቅምና የደህንነት ስርዓት ያሻሽላል።

ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድና የጉባኤው ተሳታፊዎችም ምቹ ቆይታ እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉ ስለመሆኑ ይገልጻሉ። በቦሌ ሻላ መናፈሻ አካባቢ የሚገኘው ሳውዝ ሴንተራል ሆቴል ባለቤት የሆኑት አቶ ኤራንጎ ቴራሳ እንደሚገልጹት፣ ከንግድ ስራ ባለፈ ጉዳዩን እንደ ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ቆጥረው እንግዶችን በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ይገልጻሉ፡፡

የአገልግሎት ደረጃ ለማሻሻል ይረዳ ዘንድ እና የጉዳዩን ግዝፈት እንዲገነዘቡ ሆቴሉ ከሰራተኞቻችን ጋር በስልጠና መልክ አጫጭር ውይይቶችን አካሂደናል የሚሉት አቶ ኤራንጎ፣ የእንግዶችን ደህንነት ለማረጋገጥ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅርበት እየሰሩ ስለመሆኑ ያስረዳሉ። እንግዶች ያለምንም ችግር ጉዳያቸውን እንዲከውኑም ለማገዝ መስተካከል ያለባቸውን ፈጣን እና አስተማማኝ የኢንተርኔት አገልግሎት ዝግጅት ተደርጓል። የአካባቢውን ንጽህና ለማስጠበቅ ስራዎች እየተሰሩ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡

እንደዚህ አይነት ሰፊ ዕድል የሚፈጥር ሁነት ሲገኝ ታዲያ ሆቴሎች ይህንን ጉባኤ ስኬታማ ለማድረግና የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባት በጋራ መስራት ይገባል የሚሉት ደግሞ የሞሲ ሆቴል ስራ አስኪያጅ ተረፈ ድጉማ ናቸው፡፡ እንግዶችን በአክብሮትና በፈገግታ መቀበል፣ የባህል ምግቦችንና መስተንግዶዎችን ማቅረብ ይገባልና ከወትሮ በተለየ መልኩ እየሰራንበት ነው ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት ማሻሻል፣ የደህንነት ስጋቶችን ማስወገድ፣ ከአካባቢው የጸጥታ ተቋማት ጋር እየሰሩ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡ አንድ ሆቴል ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስን ሲያስተናግድ፣ በአዳራሾቹ ጥራት፣ በሠራተኞቹ የሙያ ብቃት፣ በአገልግሎት ደረጃውና በአስተዳደር ቅልጥፍናው ትልቅ ስም ሊገነባ ይችላል። በዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና ሊያስገኝልንም ይችላል ይላሉ።

በመዲናዋ በስፋት እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር እና የወንዝ ዳር የልማት ስራዎች ለሆቴሎች እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤታማነት አስተዋፅኦው ከፍተኛ መሆኑን የሚገለፁት ደግሞ የግዮን ሆቴሎች ድርጅቶች ተወካይ አቶ በረከት መልካሙ፣ በመዲናዋ የተሰሩ የልማት ስራዎችን አድንቀው፣ የሚመጡ እንግዶችን በሞቀ የኢትዮጵያዊ አቀባበል ተቀብለው ለማስጎብኘት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። በከተማዋ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ሁነቶች እንግዶችን ከማስተናገድ ባሻገር፣ በከተማዋ የሚኖራቸውን ቆይታ ለማራዘም የሚረዱ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የሚያመላክት እንደሆነም ገልፀዋል።

ለዝግጅት ክፍላችን ሀሳባቸውን ያካፈሉ የሆቴል ባለቤቶች እንደሚገልጹት እንደዚህ አይነት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በመዲናዋ መዘጋጀታቸው በተለይም ሆቴሎች ተደጋጋሚ እንግዶችን እንዲያገኙ በር ይከፍትላቸዋል። የኮንፈረንስ ቱሪዝም ፍላጎት ሲጨምር፣ ሆቴሎች አገልግሎታቸውን ለማሻሻል ወይም አዳዲስ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ይበረታታሉ። ይህ ደግሞ በሆቴሉ ዘርፍ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ ያደርጋል። ሆቴሎች የኮንፈረንስ አዳራሾቻቸውን ያስፋፋሉ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ይተገብራሉ እንዲሁም የውስጥ አገልግሎት ደረጃቸውን ከፍ ያደርጋሉ። ይህም ሆቴሉ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስችለዋል ብለዋል።

አክለውም ጉባኤዎቹ ሲዘጋጁ ብዙ የሥራ ዕድሎች ይፈጠራሉ። ለምሳሌ የዝግጅት አስተባባሪዎች፣ የጉብኝት መሪዎች፣ አስተርጓሚዎች፣ የሆቴል ሰራተኞች፣ ሾፌሮች እና የደህንነት ሰራተኞች ያስፈልጋሉ። እነዚህም የሥራ ዕድሎች ቀጥተኛ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ተያያዥ ዘርፎችንም ያካትታሉ። ለሆቴሎች ብቻ ሳይሆን ለመዲናዋም ይዞት የሚመጣው ትሩፋት ቀላል አለመሆኑን አንሰተው፣ በዘላቂነት ዘመናዊ ሆቴሎች፣ የተሻሻሉ መንገዶች፣ የትራንስፖርት ሥርዓቶች እና የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎቶች እንዲገነቡ ያበረታታል። ይህም ለከተማዋ ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ለወደፊትም ተጨማሪ ጉባኤዎችን ለመሳብ ይረዳል ይላሉ።

ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በተሳካ ሁኔታ ማስተናገድ የከተማውንና የሀገሩን ገፅታ ከፍ ያደርጋል። ከተማዋ እንደ ዓለም አቀፍ የንግድ፣ የዲፕሎማሲ እና የባህል ማዕከል እንድትታወቅ ይረዳል። ይህም ለወደፊት ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችንና ቱሪዝምን ለመሳብ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋልና ሆቴሎች ትልቅ ኃላፊነት አለብን ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

የዓለም አቀፍ ሆቴል እና ሬስቶራንት ማህበር መረጃም እንደሚያሳየው ኮንፈረንሶች ላይ የሚሳተፉ የንግድ ተቋማትና ግለሰቦች ለሆቴሎች አዳዲስ የንግድ አጋርነቶችን ይፈጥራሉ። ለምሳሌ፡-

የጉዞ ወኪሎች፣ የጉብኝት አስጎብኚዎች እንዲሁም የሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተወካዮች ከሆቴሉ ጋር የንግድ ግንኙነት ይፈጥራሉ። እነዚህ ግንኙነቶች ወደፊት ለሚደረጉ ዝግጅቶችና ጉብኝቶች የረጅም ጊዜ ስምምነቶችን ለመፍጠር ያስችላሉ ይላል የማህበሩ መረጃ።

አንድ ትልቅ ኮንፈረንስ ሲካሄድ፣ ሆቴሎች ከወትሮው የበለጠ ሠራተኞችን የመቅጠር ፍላጎት ይኖራቸዋል። ይህ ፍላጎት ለጊዜያዊ እና ለቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል። አገልግሎት አቅራቢዎች፣ አስተናጋጆች፣ የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎች፣ የጸጥታ ጠባቂዎችና የጽዳት ሠራተኞች በተለያዩ ደረጃዎች ሥራ ያገኛሉ። ይህም የአካባቢውን የሥራ ገበያ በማነቃቃት ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል።

በሳህሉ በርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review