በዓላቱ ሴቶች አስተዳደራዊ ስርዓት የሚማሩባቸው፣ ማህበራዊ ግንኙነቶችንም የሚያዳብሩባቸው እንደሆኑ ተገልጿል
ለኢትዮጵያዊ አብሮነትና አንድነት፣ ለህዝቡ የእርስ በርስ ትስስር፣ ለማህበራዊ መስተጋብር… መሰረት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የበዓላት እሴቶች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ እሴቶች አበርክቶቸው ብሔርን፣ ጾታን፣ የዕድሜ ክልልን፣ የእውቀት ደረጃንና ሌሎችንም የማይለዩ መሆኑ ዋጋቸውን የበለጠ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተናፋቂ የሴቶች የነጻነት በዓላት የሆኑትን ሽኖዬ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና አሸንዳን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የልጃገረዶች የነጻነት በዓላት ከሆኑት መካከል ሽኖዬ አንዱ ነው። ይህም ክረምት አልፎ የፀደይ ወቅት መምጣቱን የሚያበስሩበት ጨዋታ ነው። በሽኖዬ ልጃገረዶች በተለያዩ ባህላዊ አልባሳት እና ጌጣጌጦች አምረውና ደምቀው አደባባይ በመውጣት ባህላዊ ዜማዎችን ያቀርባሉ።
በዓሉን በተመለከተ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ሀደ ሲንቄ አረጋሽ ገዳ ለዝግጅት ክፍላችን ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡ ሀደ ስንቄ አረጋሽ በማብራሪያቸው፣ “አበባ ይዘን ቤት ለቤት በመሄድ እንጨፍራለን። ዳቦ አልያም ገንዘብ ይሰጠናል፤ እንመረቃለን፡፡ በዕለቱ ቤተሰብ ‘ለምን?’ ብሎ አይቆጣንም” ሲሉ ከቀደመ ትውስታቸው ጋር በማስተሳሰር የነጻነት በዓል መሆኑን ገልጸውልናል፡፡
የበዓሉ ዕለት ልጃገረዶች በወጣቶች የሚታጩበት አጋጣሚዎች ስለሚፈጠሩ ትውውቅን ከማጠናከርና አብሮነትን ከማጎልበት አንጻር ያለው አበርክቶ ትልቅ መሆኑን አክለዋል፡፡
በዋግህምራና በሰቆጣ አካባቢዎች “ሻደይ”፣ በላስታ ላሊበላና ጎንደር “አሸንድዬ” እንዲሁም በራያ ቆቦ “ሶለል”፣ በእንደርታና ተምቤን “አሸንዳ”፤ በአክሱም “አይኒዋሪ” እንዲሁም በአዲግራት አካባቢዎች “ማርያ” የሚሰኘው ሌላኛው የሴቶች የነጻነት በዓል ነው። ሴቶች ልጃገረዶችም ሆኑ እናቶች አምረውና ተውበው የሚታዩበት፣ ከሚሰሩት ስራና የቤተሰብ ቁጥጥር ነፃ የሚሆኑበት፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ደስታቸውንና ናፍቆታቸውን በአደባባይ የሚገላለፁበት ነው። በዓሉን ሴቶች እንደ ነጻነታቸው ቀን በመቁጠር አሸንዳ የተባለውን ቅጠል ሰፊ ቄጤማ መሳይ አረንጓዴ ሳር አቀጣጥለውና እንደጉርድ ቀሚስ በወገባቸው አስረው ከበሮ እየመቱ ከንጋት እስከ ምሽት ድረስ በጨዋታ ያሳልፉታል።
የሰቆጣ ከተማ ተወላጅ እና የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ወይንሀረግ አዳነ፤ በዓሉ በጉጉት የሚጠበቅ፣ ሴቶች ነፃነታቸውን የሚያውጁበትና በአደባባይ የሚነግሱበት እንደሆነ ይናገራሉ። ‘‘በዓሉን ለማክበር ሦስት እና አራት ቀናት ሲቀሩ ከምንተዋወቃቸውና በእድሜ እኩያ የሆንን ልጃገረዶች ተሰባስበን ቡድን እንመሰርታለን፤ ሹሩባ እንሰራለን፤ በዋዜማውም ከስር ነጭ ከላይ አረንጓዴ የሆነውን የሻደይ ቅጠል ቆርጠን እንመጣለን፡፡ ከዚያም ወገብ ላይ ለማሰር በሚመች መልኩ እንሰራለን” ሲሉ ለበዓሉ ስለሚያደርጉት ቅድመ ዝግጅት ይገልፃሉ።
ነሐሴ 16 ቀን በጠዋት አዳዲስ ልብስና ጫማ በመልበስ፣ አሸንዳውን ወገባችን ላይ እንታጠቃለን፡፡ ከዚያም የሃብታምና የድሃ ሳይባል በሁሉም ቤት እየገባን በነፃነት እንጨፍራለን፤ እንጫወታለን። ይህ ሂደትም እስከ አራት ቀን ድረስ ይቀጥላል፡፡ በአራተኛው ቀን ቤተ ክርስቲያን በመሄድ የተሰጠንን ምግብ በመመገብ ለቀጣይ ዓመት “በሰላም አድርሰን” ብለን ጨዋታችንን እንቋጫለን ሲሉ ስለበዓሉ አከባበር ተናግረዋል፡፡
“በዓሉ ለእኔ ትልቁ የነፃነቴና የደስታዬ ቀን ነው” የሚሉት ወይዘሮ ወይንሀረግ፤ “ከዝግጅቱ ጀምሮ በዓሉ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ ማንኛውም የቤተሰብ አባል ‘የት ወጣሽ፣ የት ገባሽ’ የሚል ቁጥጥርና ቁጣ ሳይኖር ውሃ ከመቅዳት፣ እንጀራ ከመጋገር፣ ወጥ ከመስራት በአጠቃላይ ከቤት ውስጥ ስራ ነፃ ሆነን በደስታና በጨዋታ የምናሳልፈው ቀን በመሆኑ ነው” ሲሉ ምክንያቱን አብራርተዋል፡፡
ይህን እንደሚናፍቁት የሚናገሩት ወይዘሮ ወይንሀረግ፣ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም በድምቀት ያከብሩታል፡፡ ለአንድ ዓመት ሳያገኙ ከቆዩት ጓደኛና ከተለያዩ የበዓሉ ተሳታፊዎች ጋር መገናኘትና መተዋወቅ አብሮነትን እና አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ዓለም አብርሃ የአሸንዳ በዓል አከባበርን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ደግሞ፣ ‘‘በዓሉ መከበር የሚጀምረው ነሐሴ 16 ሲሆን፤ እስከ ነሐሴ 18 ቀን በድምቀት መከበሩን ይቀጥላል፡፡ በልጃገረዶች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ፣ የነፃነትና የደስታቸው ቀን ነው፡፡ በዓሉ ከመከበሩ አስቀድሞ ፀጉራቸውን ይሰራሉ፤ ባህላዊ አልባሳት ገዝተው፣ ያላቸውን አጥበው ወይም ከጎረቤት አሊያም ከዘመድ ተውሰው ይጠቀማሉ” ሲሉ ነግረውናል፡፡
ወይዘሮ ዓለም አክለውም፣ “በዋዜማው የሚደረገው አሸንዳውን የማዘጋጀት ስራ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ የበዓሉ እለት ደግሞ ተሰባስበው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እለቱን በምስጋና ያሳልፋሉ፡፡ በእያንዳንዱ ቤት በመሄድ ደግሞ ያዜማሉ” በማለት ስለክዋኔውና እሳቸውም ይኼንኑ ያደርጉ እንደነበር በማስታወስ ነግረውናል፡፡
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ እዮብ ዘውዴ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፤ ‘‘ሻደይ ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴትን አጣምሮ የያዘ በየዓመቱ ከነሐሴ 16 እስከ 21 ቀን በታላቅ ድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ የበዓሉ ዋነኛ ባለቤቶችም ህፃናት፣ ወጣት ልጃገረዶች እና እናቶች ናቸው፡፡’’ ብለዋል፡፡
አቶ እዮብ አያይዘው እንደተናገሩት፤ በበዓሉ ሴቶች አምረው፣ ደምቀውና ተውበው በአደባባይ ይታያሉ። በተለየ ሁኔታ እናቶች ለህፃናቱና ልጃገረዶች ስለ በዓሉ አከባበር ስርዓት የሚያሳውቁበትና ባህሉም ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚያደርጉበት ነው፡፡ በእነዚህ ቀናት ሴቶች ከምንም ዓይነት ቁጥጥር ነፃ ሆነው የሚጫወቱበት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ራሳቸውን ማዘዝ፣ መምራት ኃላፊነት መውሰድና በትብብር መስራትን የሚለምዱበትም ነው፡፡ ይህም ነፃነታቸውን የሚያውጁበት ማለት ነው፡፡
የአሸንዳ በዓል ሴቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ፣ ሀሳባቸውን መግለጽ እንዲችሉ፣ አቅም እንዳላቸው እንዲረዱና ለተለያየ ተልዕኮ ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ነው፡፡ ሴቶች በዓሉን ለማክበር ከቤት የወጡበትን ዓላማ ከውነው በታማኝነት መመለሳቸው፤ በተሰማሩበት የአመራርነትም ይሁን የሙያ ዘርፍ ምን ያህል ታማኝና ብቁ መሆናቸውን የሚያሳዩበት ነው ሲሉም በዓሉ ለሴቶች ያለውን ትርጉም አስረድተዋል፡፡
የሀደ ሲንቄ አረጋሽን ሀሳብ የሚያጠናክሩት ግርማ በቀለ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ግርማ (ዶ/ር) በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህርና የአንቦ ዩኒቨርሲቲ የርቀት ትምህርት አስተባባሪ ናቸው፡፡ በዩኒቨርስቲው ፎክሎርና የቋንቋ ብዝሃነትን ሲያስተምሩም ቆይተዋል። ዶክተሩ በማብራሪያቸው፣ “ሽኖዬ፤ ልጃገረዶቹ በባህላዊ አለባበስ በማጌጥ፣ የልምላሜ መገለጫ የሆኑ ሳር ወይም እንግጫ ይዘው በአደባባይ መውጣታቸው ነፃነታቸውን የሚጎናፀፉበት ማሳያ ነው። በዓሉ ክረምቱ አልፎ ለአዲሱ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን የሚገልፁበት ነው። ልጃገረዶቹ በአደባባይ ሃሳባቸውን በግጥም የሚገልፁበት፣ እርስ በእርሳቸው የወደፊት ተስፋቸውንና ህይወታቸውን በግልፅ የሚመካከሩበትና የሚማማሩበት፣ ማመስገን እንደሚችሉ የሚያውቁበት ነው” ብለዋል፡፡
አክለውም፤ “ልጃገረዶቹ ይህንን በዓል ለማክበር ሲወጡ የወደዱትን (ያፈቀሩትን) በግልፅ መናገር ባይችሉም በግጥሞቻቸው የማመስገን እና ፍላጎታቸውን የሚገልጹበት ነው፡፡ የትዳር አጋራቸውንም የመምረጥ እድል የሚያገኙበትና ማስተዳደር እንደሚችሉ የሚረዱበት በመሆኑ ትልቁ ነፃነታቸው ነው፡፡
የልጃገረዶች የእኩልነታቸው፣ የአንድነታቸው መገለጫ የሆነው የሽኖዬ በዓል ለትውልድ እንዲተላለፍ ታሪኩን፣ እሴቱንና ወጉን በጠበቀ ማክበሩን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ልክ እንደ ሽኖዬ ሁሉ አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል በዓል ልጃገረዶች በአደባባይ ደምቀው የሚታዩበት በዓል መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህር አስቴር ሙሉ (ዶ/ር)፣ በዓሉ ነሐሴ ሲገባ ጀምሮ ዝግጅት የሚደረግበትና ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ ደግሞ እንደየአካባቢው ሁኔታ ልምድና ስርዓት የሚከናወን ነው” ይላሉ፡፡
እንደ ፎክሎር መምህሯ ገለጻ፣ የበዓሉ ክዋኔ፤ ልጃገረዶች ካላቸው የራሳቸውን፣ ከሌላቸው ደግሞ ከጎረቤቶቻቸው ወይም ከታላላቅ እህቶቻቸው በመውሰድ በተለያዩ አልባሳት፣ የፀጉር ስራ፣ ጌጣጌጦች አምረውና ተውበው የሚታዩበት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ሴቶቹ ያገባች ያላገባች፣ የታጨች ያልታጨች የሚለውን የአለባበስ ስርዓትና ባህል አስጠብቀው የሚያሳዩበት ነው፡፡
ልጃገረዶቹ ክዋኔውን የሚጀምሩት ከቤተ ክርስቲያን መሆኑን የነገሩን መምህርቷ፤ ከዚያም አመስግነው ሲመለሱ እንደየ ማህበረሰቡ ደረጃ ከትልልቅ አባቶች ቤት በመጀመር በሁሉም ቤት በመሄድ በድምቀት ያከብሩታል፡፡
በኢትዮጵያ ባህል ሴት ልጆችን ከአደጋ ከመጠበቅ፣ ስርዓት ከማስተማር፣ የወላጆችን አኗኗር እንዲማሩ ከመፈለግ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ውጭ ስለማያስወጧቸው እንደዚህ ክብረ በዓል ነፃነታቸውን የሚያገኙበት ቀን የለም፡፡ በዚህ ቀን በነፃነት በአደባባይ ይዘምራሉ፣ ይዘፍናሉ፣ ማህበረሰቡን ያወድሳሉ፡፡ ከማህበረሰቡም የሚሰጣቸውን ስጦታ በባህሉና ትውፊቱ መሰረት ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡበትም በዓል ነው፡፡
አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል በዓል ሴቶች ለበዓሉ ሲዘጋጁ እርስ በእርሳቸው የሚመራረጡበት በመሆኑ አስተዳደራዊ ስርዓትን ይማሩበታል፡፡ አብረው ሲውሉ ደግሞ አብሮነትን፣ መቻቻልን፣ አብሮ ያገኙትን መካፈልንና የመሳሰሉትን ማህበራዊ ግንኙነቶችን ያዳብሩበታል፡፡
በዓሉ ልጃገረዶች ከቤት ባሻገር ውጭ ላይ ያለውን የአካባቢያቸውን ሁኔታ የሚያዩበት፣ በግጥሞቻቸው ውስጥ የራሳቸውን ማንነት የሚገነቡበት፣ በራስ መተማመናቸውን የሚጨምሩበት፣ የግል ፍላጎታቸውን የሚያንፀባርቁበት ክብረ በዓል በመሆኑ ነፃነታቸውን ለማወጅ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህ የፎክሎር ሃብት ልጆቹን ለመጭው ህይወት እንዲዘጋጁና ኃላፊነትን እንዲወስዱ የሚያደርግ፣ ለወደፊት ነገሮችን የሚረዱበትንና የሚለምዱበትን መንገድ የሚያሳይ በመሆኑ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል በማድረግ በኩል የራሱ ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተዋል፡፡
ይህ የበዓል ክዋኔ የማህበረሰቡ ማንነት፣ ስነ ልቦናው ምን እንደሚመስል የሚታይበት በመሆኑ የማህበረሰብ ማንነት የሚያስጨንቀው ማንኛውም አካል ለልጆች መሰረታዊ የሆኑትን ነገሮች በማስጨበጥ እና ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን በማስቀጠል ተልዕኮውን እንዲወጣ ሲሉ አደራ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ሁለቱ ምሁራን እንደገለጹት በዓላቱ የሴቶችን ነጻነት ከማጎናጸፍ አንጻር አበርክቷቸው ትልቅ በመሆኑ አጠንክሮ ማስቀጠል ከሚመለከታቸው አካላት ይጠበቃል መልዕክታችን ነው፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ