የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ለስድስት አስርት ዓመታት የመጣበት መንገድ ሲታወስ፣ ከፊት የሚጠቀሱ አንጋፋ ስሞች መኖራቸው አይቀሬ ነው። ከእነዚህ መካከል አርቲስት ደበበ እሸቱ አንዱ ነው። የክብር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ በ60 ዓመታት የጥበብ ህይወቱ፣ በርካታ ድራማዎች፣ ፊልሞች እና ቴአትሮች ላይ በመተወን በኢትዮጵያ የጥበብ ታሪክ የማይረሳ አሻራውን አኑሯል፡፡ ወጣቶችን በመቅረጽ እና ልምድን በማካፈል ለኪነ ጥበብ እድገት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ከአርቲስት ደበበ እሸቱ ጋር በአንድ መድረክ በተደጋጋሚ ከተወኑና አብረው ከሰሩ የጥበብ ባለሙያዎች መካከል ቢኒያም ብርሃኑ ተጠቃሽ ነው፡፡ ቢኒያም ዘወልድን፣ ሀገር ማለትን፣ ጎህ ሲቀድን፣ የብርሃን መንገድን፣ የሀገር ብሌንን ጨምሮ ከ18 በላይ ቴአትሮች ላይ ሰርቷል፡፡ መላ፣ የእኔ መንገድ፣ ጉዞ፣ ዘዴ፣ ሙሽሪት፣ ጥቁር ጉንዳ፣ ንጉስ ቆስጠንጢኒዮስ እና ሌሎችም ፊልሞች ላይ በድርሰት፣ በዳይሬክተርነትና በተዋናይነት ተሳትፏል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል እንዲሁም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተጋባዥነት የቴአትር ትምህርት ያስተምራል፡፡ ሌሎች በርካታ የኪነ ጥበብ ስራዎችን በማዘጋጀትም ይታወቃል። ይህ የጥበብ ስራው ደግሞ ከአርቲስት ደበበ እሸቱ ጋር ወዳጅ አድርጎታል። ከቅርበታቸው አንጻርም ሲጠራው አርቲስት ደበበ ሳይሆን “ጋሼ” እያለ ነው፡፡ አርቲስት ደበበ እሸቱና ቢኒያም “ከፈተና ወደ ልዕልና” የሚል ቴአትር በጋራ ሰርተዋል፡፡ የእርቅ መርሃ ግብር ላይም በጋራ ተውነዋል፡፡ “ነቢይ ዤሮ” የተሰኘው ቴአትር ደግሞ ሌላው በጋራ የተወኑበት የጥበብ ስራ ነው፡፡
ቢኒያም ከአርቲስት ደበበ እሸቱ ጋር የተገናኘነው በስራ አጋጣሚ ነው፡፡ የኪነ ጥበብ ስራ ለመስራት ከተገናኘን በኋላ እጅግ ሰው አክባሪና ቅን የኪነ ጥበብ ሰው መሆኑን ተረዳሁ፡፡ እውነተኛ የጥበብ ሰው መሆኑ ከሚታወቅበት አንዱ ሰው አክባሪነቱ ነው፡፡ አርቲስት ደበበ የኪነ ጥበብ መድረክ ላይ የክብር እንግዳ አድርገን ስንጠራው በፍጹም ቅንነት ይገኛል፡፡ ደስ የሚልና ልዩ ሰው ነበር ይላል፡፡
በቀላሉ ከሰው ጋር መግባባት የሚችል ነው፡፡ ከአንጋፋና ወጣት ባለሙያዎች ጋር ስራን መስራት ይችልበታል፡፡ ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ በሀገራችን ኪነ ጥበብ ውስጥ የማይዘነጋ አሻራውን አኑሯል። ከሀገራችንም አልፎ በሆሊውድ ደረጃ መስራት የቻለ ሰው ነው፡፡ ለዚህም “ሻፍት ኢን አፍሪካ” የተሰኘውን ፊልም መጥቀስ ይቻላል ሲል ይጠቅሳል፡፡
“አርቲስት ደበበ እሸቱ በኪነ ጥበብ መድረክ ሁሉ ወጣቶችን በማነቃቃትና ተስፋ በማሳየት ይታወቃል፡፡” በማለትም ቢኒያም አብራርቷል፡፡
አርቲስት ደበበ እሸቱ ተፈጥሯዊ የሆነ የትወና ችሎታ የነበረው ሲሆን፤ የሚተውናቸውን ገጸ-ባህሪያት ማንነት በመላበስ ተመልካችን መማረክም ችሏል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ቴአትር እና በተለያዩ የፊልም ስራዎች ላይ የነበረው ድርሻ እጅግ የጎላ ነው። በርካታ ተውኔቶች እና የሀገራችን ፊልሞች ላይ ተሳትፎ በማድረግ፣ በብዙ አድናቂዎቹ ልብ ውስጥ ለዘላለም የሚኖር ትውስታ ጥሎ አልፏል፡፡
የአርቲስት ደበበ እሸቱ የጥበብ ሰውነት ከትወና ችሎታም ባሻገር ነበር የሚለው ቢኒያም፣ ስለ ጥበብ ያለው ግንዛቤ ስፋትና ለሀገር ፍቅር ያለው ስሜት የተለየ ነበር። ይህንንም ወደ ሌሎች አርቲስቶች በማስተላለፍ ለብዙዎች መምህር እና አማካሪ ሆኖ ያገለገለ ሰውም ነበር፡፡
የኢፌዴሪ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ፣ ስነ ጥበብና ፈጠራ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ እና የአዲስ አበባ ባህል እና ኪነ ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) የሰጡት ምስክርነትም የቢኒያምን ሃሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡
ነብዩ ባዬ፣ “በእውቀት ፍለጋ ጥማት እና ትምህርት፣ በሙያ ሥነ ምግባር፣ ባመነበት በመቆም ጽናት አብሬው ሰርቼ ተጠቅሜያለሁ። በልጅነት አዘጋጁ ሆኜ እሱ ግዙፉ ተዋናይ ሆኖ ስንሰራ ያየሁት ሙያ አክባሪነት ስንቄ ሆኗል” በማለት ሲገልጹት፣ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው ደበበ እሸቱን ስመጥር የጥበብ ሰው በማለት ገልጸውታል፡፡
ቢኒያም እንደተናገረው፣ አርቲስት ደበበ እሸቱ የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ታሪክ አካል ነው። የዘመኑን የቴአትር እና የፊልም ጥበብ መሰረት የጣለ እና ለቀጣይ ትውልድ አርቲስቶች ታላቅ አርአያ የሆነ የጥበብ ሰው ነበር። እሱ ለጥበብና በጥበብ አማካኝነት ለሀገር ያበረከተው የማይረሳ አስተዋጽኦ ለዘላለም የሚታወስ ይሆናል።
ለአርቲስቱ ከተበረከቱ ሽልማቶች በጥቂቱ
አርቲስት ደበበ እሸቱ ዘመን ተሻጋሪ ሃሳቦችንና ስራዎችን አበርክቶ አልፏል። ዋናው ጉዳይ አርቲስቱ በመጪው ትውልድ ዘንድ እንዲታወስ ከስራዎቹ በተጨማሪ ምን መደረግ አለበት የሚለው ነው፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሙያው ቢኒያም ብርሃኑ በሌላው ዓለም አንጋፋ አርቲስቶች በህይወት እያሉ ጭምር መታወሻዎች ይሰሩላቸዋል፡፡ አደባባዮች በስማቸው ይሰየማሉ፡፡ ሐውልት ይሰራላቸዋል፡፡ እኛ ሀገር ይህ ባህል ብዙ አልተለመደም ይላል፡፡
የደበበ እሸቱ ስራዎች ከመቃብር በላይ ናቸው፡፡ አበርክቷቸውን ለመግለጽና ለማክበር የጥበብ ትምህርት ቤቶች በስሙ ቢሰየሙ እንዲሁም ጎዳናዎች በደበበ ስም ቢሰየሙ ያንሳል እንጂ አይበዛበትም ሲልም ሃሳቡን አንስቷል፡፡
በእርግጥ ደበበ እሸቱ በህይወት ሳለ በርካታ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን አግኝቷል፡፡ ለአፍሪካ ቴአትር ባደረገው አስተዋጽኦ የዚምባብዌን ማላካይት አዋርድ ተሸላሚ ነበር፡፡ ጣይቱ ኢንተርቴይመንት በዋሽንግተን ዲሲ በቴአትር ዘርፍ የህይወት ዘመን ሽልማት አበርክቶለታል፡፡ የጥበብ ሰዎችን ታሪክ በመሰነድ የሚታወቀው ተወዳጅ ሚዲያ እንዳሰፈረው ደግሞ፣ በአትላንታ ጆርጂያ የከተማው ምክር ቤት ለዓለም ቴአትር ላደረገው አስተዋጽኦ ኖቬምበር 24ን “የደበበ እሸቱ ቀን” በሚል ሰይሞታል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ባህል ሚኒስቴርም ደበበ እሸቱን ለኢትዮጵያ ፊልም እድገት ላበረከተው አስተዋጽኦ ሸልሞታል፡፡ በጉማ አዋርድ ደግሞ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ነበር፡፡ በተጨማሪም እ.ኤ.አ በ2015 በቫንኮቨር ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል በምርጥ መሪ ተዋናይ ዘርፍ አሸናፊ በመሆን ተሸልሟል፡፡ በ2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ባበረከተው አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አበርክቶለታል፡፡
የአርቲስቱ ሙያዊ አበርክቶ
ክቡር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ ከ40 በላይ ተውኔቶች ላይ ተሳትፏል። ከተወነባቸው ቴአትሮች መካከል እናት ዓለም ጠኑ፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ ኪንግ ሊር፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ናትናኤል ጠቢቡ፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ የከርሞ ሰውና ጠልፎ በኪሴ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
የመንግስቱ ለማን “ጠያቂ”፣ የተስፋዬ ገሰሰን “ተሐድሶ”፣ የአያልነህ ሙላትን “ሻጥር በየፈርጁ”፣ የነጋሽ ገብረማርያምን “የአዛውንቶች ክበብ” እና የዊልያም ሼክስፔርን (የመስፍን አለማየሁ ትርጉም) “ሊር ነጋሲን” (በኋላም “ንጉሥ ሊር”) ጨምሮ 28 ተውኔቶችን አዘጋጅቶ ለእይታ ማቅረቡን የተወዳጅ ሚዲያ እና ህልፈታቸውን አስመልክተው ዘገባ ከሰሩ መገናኛ ብዙሃን መረዳት ይቻላል፡፡
በተዋናይነትና ተርጓሚነት ከተሳተፈባቸው በርካታ የመድረክ ሥራዎቹ ውስጥ ያላቻ ጋብቻ፣ ሮሚዎና ዡልየት፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ የበጋ ሌሊት ራዕይ፣ አንድ ዓመት ከአንድ ቀን፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ በቀይ ካባ ስውር ደባ፣ ተሓድሶ፣ ኪንግ ሊር፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ የወፍ ጎጆ፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ ናትናኤል ጠቢቡ፣ ድብልቅልቅ፣ ጠልፎ በኪሴ፣ ጠያቂ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ ዘ ጌም ኦፍ ቼዝ (በእንግሊዝኛ)፣ አዳ ኦክ አራክል (በእንግሊዝኛ)፣ ኦቴሎ (በእንግሊዝኛ) ይጠቀሳሉ፡፡
በዓለም አቀፍ የሲኒማ ጥበብ ትወና በብዛት ከተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ቀደምት የሆነው ደበበ በፊልም ስራም በኢትዮጵያውያን የተዘጋጁ የተለያዩ የሀገር ውስጥ ፊልሞችን ጨምሮ ከሪቻርድ ራውንድትሪና ከሰር ፍራንክ ፊንሊ፣ ከቴሬንስ ስታምፕ፣ ከጃን ሞንሮና ከሂዩ ግሪፍዝ፣ ከሶፊያ ሎሬን ጋር የተወነባቸው ፊልሞች “ሻፍት ኢን አፍሪካ”፣ “ዘ አፍሪካን ስፓይ”፣ ”ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብራልታር”፣ “ኤ ሲዝን ኢን ሔል”፣ “ዜልዳ”፣ “ዘ ግሬቭ ዲገር”፣ “ዘ ግራንድ ሪቤሊየን”፣ ሬድ ሊቭስ “ጉማ” በሚሉት ላይም ተሳትፏል፡፡
በስነ ጽሑፍ ዘርፍም “የተዋናይ ሀሁ” መጽሐፍ ለበርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች የሙያቸው ፊደል መቁጠሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከትርጉም ሥራዎቹ የሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “የደም እንባ” መጽሐፍ፣ “ድብልቅልቅ የመድረክ ተውኔት”፣ “ያልታመመው በሽተኛ” እና ሌሎችንም ስራዎች ወደ አማርኛ ተርጎሟል አበርክቶው ከትወና የተሻገረ እንደነበር ማሳያ ነው፡፡
በተጨማሪም ደበበ እሸቱ የአፍሪካ መድረክ ባለሙያዎች ማህበር መስራች፣ የዓለም ኮንቴምፖራሪ ቴአትር ኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባል፤ የዓለም አቀፍ ቴአትር ኢንስቲትዩት የአፍሪካ አስተባባሪና የኢትዮጵያ ተጠሪ፤ በብሔራዊ ቴአትር የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ኃላፊ፤ በሀገር ፍቅር ቴአትር የኪነ ጥበብ አገልግሎት ኃላፊ፣ በራስ ቴአትር ዋና ስራ አስኪያጅነት፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በርካታ ማህበራዊ፣ የልማትና እርዳታ አገልግሎቶች ላይ አስተባባሪ፣ የሰላምና እርቅ ኮሚቴ አባል፣ የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል አምባሳደር፣ በኩላሊት ሞት ይብቃ አምባሳደር በመሆን ያደረገው አስተዋጽኦ ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳል፡፡
አርቲስት ደበበ እሸቱ የተወለደው በ1934 ዓ.ም አዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የተከታተለ ሲሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፐርፎርሚንግ አርትስ ተምሯል። እ.ኤ.አ በ1965 ደግሞ ወደ ሃንጋሪ በማቅናት የቴአትር ጥበብን አጥንቷል። ወደ ሃንጋሪ ከማቅናቱ በፊት በ1964 ዓ.ም ከወ/ሮ አልማዝ ደጀኔ ጋር ትዳር መስርቶ 4 ልጆችንና 8 የልጅ ልጆችን አፍርቷል።
ህልፈት
የክቡር ዶክተር ደበበ እሸቱ ህልፈተ ዜና የተሰማው ባሳለፍነው እሑድ ነሐሴ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ነበር፡፡ በተወለደ በ83 ዓመቱ ያለፈው ደበበ የቀብር ሥነ ስርዓቱ ባሳለፍነው ማክሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ቤተሰቡ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የሙያ አጋሮቹና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ የክብር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ የትወና ችሎታው፣ ስለ ኪነ ጥበብ የነበረው ጥልቅ ግንዛቤ እና በስራዎቹ የፈጠረው አይረሴ አበርክቶ ለጥበብ ዓለም ትቶት የሄደው ሀብት ነው።
በጊዜው አማረ