ተሻጋሪው ኃላፊነት

You are currently viewing ተሻጋሪው ኃላፊነት

የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ34 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በውስጡም ከህክምና ጋር የተያያዘ አገልግሎት የሚሰጡ እድሜ ጠገብ ህንፃዎች አሉ፡፡ ከሕንፃዎቹ እና ከቅጥረ ግቢው ጋር በተጣጣመ መልኩ የተተከሉ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ዛፎችም ይገኛሉ፡፡ ወደ ቅጥር ግቢው ውስጥ እግር ጥሎት የተገኘ ሰው በቅድሚያ አይኑ የሚያርፈው፤ በተዋበው የአትክልት ስፍራዎቹ ላይ ነው፡፡ የግቢው አትክልት ለታመመ፤ ሕመሙን አስረስቶ የጤና እስትንፋስን የሚቸር፣ ለግቢው ማህበረሰብ ደግሞ መልካም የሥራ ከባቢን የሚያድል ነው፡፡ በአግባቡ በተዘጋጀው የአትክልት ሥፍራ የተተከሉ እፅዋት ለጥላ፣ ለምግብነት ብሎም ለመድኃኒትነት አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸው ደግሞ አንጋፋው የጤና ተቋም ለዘርፉ የሰጠውን ከፍ ያለ ትኩረት አመላካች ነው፡፡

ፅዱ፣ ምቹ እና ለሥራ ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢን መፍጠር ለነገ የሚባል ተግባር እንዳልሆነ የሚናገሩት የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሽመልስ ገዛኸኝ፤  “ሁሉን አቀፍ አገልግሎት እየሰጠ መገኘቱን ተከትሎ ለአረንጓዴ ልማት ሥራዎችም የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ተቋሙ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን በስፋት ማከናወን የጀመረው ከአራት ዓመት በፊት ነው፡፡  ዛሬ ላይ ይህ ሥራ እንደሆስፒታል ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ፤ የተንጣለለውን የሆስፒታሉን ቅጥር ግቢ በአግባቡ መጠቀም መቻሉ ነው” በማለት አብራርተዋል፡፡

እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለፃ፤ በሆስፒታሉ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ዛፎች አሉ፡፡ ከአራት ዓመት ወዲህ ተግባራዊ በተደረገው ተቋማዊ አረንጓዴ ልማት ሥራም አዳዲስ ዕፅዋት ተተክለዋል፤ በባለሙያ የታገዘ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል። የእንክብካቤውን ሂደት የሚከታተል እና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ግብረ ሃይልም ተቋቁሟል፡፡  የውሃ አቅርቦት ችግር ቢያጋጥም እንኳን በቦቴ በማቅረብ የእፅዋቱ እንክብካቤ ሳይቋረጥ የሚቀጥልበት አሠራር እንደባህል ተይዞ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

ለሀገር በቀል ዕፅዋት ትኩረት የሚሰጠው ሆስፒታሉ፤ በቅጥረ ግቢው ከተተከሉት ዕፅዋት መካከል፡- እንደ ወይራ፣ ብርብራ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ የመሳሰሉ ሀገር በቀል ዛፎች በስፋት ይገኛሉ።  ከዚህ በተጨማሪም፤ እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ዘይቱና የመሳሰሉትን ለምግብነት የሚውሉ አትክልቶችን በመትከል ከፍሬያቸው መጠቀም ተጀምሯል፡፡ በተጨማሪም ለህክምና አገልግሎት ጥቅም ከሚሰጡ እፅዋት ጭምር አስፈላጊው ውጤት መገኘቱን የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አብራርተዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ አክለው እንደገለጹት፤ በሆስፒታሉ ቁጥራቸው 30 የሚሆኑ የጉልበት ሰራተኞች ችግኞችን በማረም፣ በመኮትኮት እንዲሁም ውሃ በማጠጣት ሥራ ተሰማርተዋል፡፡ የዕፅዋትን እንክብካቤ ሂደት የሚከታተለው እና የሚቆጣጠረው ግብረ ሃይል ሚናም፤ የአተካከል ችግር ያለባቸውን የማስተካከል፣ በበጋ ወቅትም እፅዋቱ ያሉበትን ደረጃ በቅርበት የመከታተል፣ የፅድቀቱን ውጤታማነት በዞን በዞን በመከፋፈል ተከታታይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡

ዶክተር ሽመልስ አክለውም፤ “የሆስፒታሉ አመራርና ሠራተኛ በቅጥር ግቢ ያልተወሰነ የአረንጓዴ ልማት ተሳትፎ አላቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኘው የሸገር ከተማ አስተዳደር በመጓዝ፤ በኤጀሬ እና በሆለታ አካባቢ በመገኘት ችግኞችን ተክለናል፡፡ በእንጦጦ አካባቢ ለጤና ሚኒስቴር በተሰጠው የመትከያ ቦታ ላይ ሆስፒታሉ ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆኑን ቀጥሎበታል፡፡ በአራት ዓመታት ውስጥም ሆስፒታሉ በሠራቸው የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በጤና ሚኒስቴር እንዲሁም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት እውቅና ተሰጥቶታል” ብለዋል፡፡

ሌላው በተለይ ሀገር በቀል ዛፎችን፣ የፍራፍሬ ተክሎችን ጨምሮ የተለያዩ ዕፅዋትን በስፋት እያለማ ያገኘነው የአዲስ መንደር የጋራ መኖሪያ ቤት ባለንብረቶች ማህበር ነው፡፡ ማህበሩ  ከአያት አደባባይ ወደ መቄዶንያ የአዕምሮ ሕሙማንና የአረጋዊያን ማዕከል  በሚወስደው መንገድ በስተቀኝ ይገኛል፡፡ በ20 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በነዋሪው የጋራ ተሳትፎ እያለማ ይገኛል።  እንደ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ካሮት፣ ቲማቲም እና ድንች ያሉትን በስፋት እያመረተ ነው። የተሰበሰበውን ምርት ደግሞ ለመንደሩ ነዋሪዎች በፍትሐዊነት ያሰራጫል፡፡ ቁጥራቸው አንድ ሺህ የሚሆኑ የሙዝ፣ ኢንጆሪ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ብርቱካን፣ ሎሚ እና ቡና ዝርያዎችን ተክሏል፡፡

አቶ ሰለሞን ፀሐይ የማህበሩ ሰብሳቢ እና በማህበሩ የአረንጓዴ ልማት አምባሳደር ናቸው፡፡ “አረንጓዴ ሥፍራ እኔነቴን ይስበዋል” የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ እያንዳንዱ ነዋሪ ሀገር በቀል የሆኑ የጥላ ዛፎችን በመትከል እንዲሁም ደግሞ ግቢያቸውን ለማሳመር የውበት ተክሎችን ጭምር እንዲተክሉ በኮሚቴዎች ክትትል ይደረጋል፡፡ ማህበሩ ይህን የመሰለ የአረንጓዴ ልማት ሥራ በመኖሪያ ግቢው ውስጥ እንዲሁም በአካባቢው ላይ የመትከል ተግባሩን የጀመረው በ2011 ዓ.ም. ነው፡፡  ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የማህበሩ አባላት ጥሩ ተሳትፎ በማድረግ ሥራውን አስቀጥለውታል፡፡ በየጊዜው ለተክሎች ያለንን አመለካከት በማሳደግ መሻሻሎችን ማሳየት ተችሏል፡፡ የሚታይ ለውጥ እንድናመጣም የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት በቅርበት በመሆን ሙያዊ ድጋፍ እንዲሁም የዘር አቅርቦትን በማመቻቸት ጭምር ተገቢውን እገዛ አድርጓል” ብለዋል፡፡

“የተተከሉ ችግኞችን የፅድቀት መጠን ከዚህ በላቀ ከፍ ለማድረግ በበጋም ጭምር ሳይቋረጥ ይፈፀማል። በበጋ ወቅት ዕፅዋቱን ለመንከባከብ አካባቢያችን ከሚገኘው ወንዝ እንዲሁም የራሳችን የጉድጓድ ውሃ በማውጣት እንጠቀማለን።” የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ የማህበሩ አባላት ስድስት ቋሚ አትክልተኞችን ቀጥረው እያሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ማህበሩ በሰራቸው የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የተለያዩ እውቅና እና ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ በወረዳ እና በክፍለ ከተማ ደረጃ በአረንጓዴ ልማት ሥራው በተደጋጋሚ ሞዴል ተደርጎ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአካል በመገኘት ያደረጉትን ጉብኝት እና የሠጧቸውን ማበረታቻ የማህበሩ አባላት የማይዘነጉት መሆኑን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የአረንጓዴ ቦታዎች አያያዝ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አጥናፉ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስረዱት፤ ከተማዋ በሁሉም መዳረሻዎች በምታከናውናቸው ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ በመሪ ፕላን መሰረት የአረንጓዴ ልማትም ተቀናጅቶ እየተተገበረ ይገኛል፡፡  የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን፣ የዘላቂ ማረፊያ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን በውበት ሚዛን እየለካ ለከተማዋ የአረንጓዴ ገፅታ ግንባታ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የሚሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ሲሳይ ገለፃ፤ በከተማዋ መዋቅራዊ ማስተር ፕላን መሰረት 30 በመቶ የሚሆነው ቦታ ለአረንጓዴ ልማት የተመላከተ ነው፡፡ የለሙ አረንጓዴ ስፍራዎችን ሙሉ ለሙሉ አረንጓዴነታቸውን አስቀጥሎ መሄድ የቢሯችን ተልዕኮ ነው፡፡ ካለፉት ዓመታት በተለየ ሁኔታ ፅድቀቱ ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡ ለዚህም ዘላቂነት ያለው የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በስፋት ለመስራት ያስችል ዘንድ ለከተማዋ ተስማሚ የሆኑ ዝርያዎችን እንደ አየር ንብረቱ ባህሪ በማጥናት ችግኞችን በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የችግኝ ጣቢያዎችን በማቋቋም የማፍላት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

አረንጓዴ ቦታዎችን ከመንከባከብ አንፃር ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴነታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ የሳር ክርከማ፣ የአረም ማረም፣ ኩትኳቶ፣ ለም አፈር በማኖር፣ ማዳበሪያ ለሚያስፈልገው እንዲሁ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ፅድቀቱ ላይ በስፋት እየተሰራ ነው፡፡ በበጋ ወቅት የተተከሉ ችግኞች እንዳይደርቁ በተለይም የውሃ እጥረት እንዳይገጥም የጉድጓድ ውሃን በፓንፕ በመሳብ ተክሎች ውሃ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። በተጨማሪም በውሃ ማጠራቀሚያ ውሃ በመሙላት እና በውሃ ቦቴዎች አማካኝነት የማጠጣት ስራ በባለሙያዎች የሚሰራ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

ዕፅዋትን የማልማት ስራ ከተሰራ በኋላ የመፅደቅ ሂደቱን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ምልከታ ይደረጋል። ለክትትል ያመች ዘንድ የአረንጓዴ ቦታን በባለቤትነት ለማልማት ፍቃድ የሚሰጣቸው ግለሰቦች አልያም ተቋማት የውል ሰነድ ይፈራረማሉ፡፡ እፅዋትን ለማልማት፣ ለመንከባከብ እንዲሁም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት የሚገልፅ ውል ከተፈራረሙ በኋላ በኃላፊነት ወስደው ያለማሉ፡፡ በተዋረድ ያለው የስራ ክፍልም በቼክ ሊስት ይገመግማል፡፡ ያልፀደቁ የደረቁ ችግኞችን በባለቤትነት ሲንከባከብ የነበረው አካል መልሶ ችግኙ ወደነበረበት አረንጓዴነቱን እንዲያስጠብቅ ይደረጋል፡፡ ኃላፊነት ወስዶ የሚንከባከበው አካል የገጠመውን ችግር መነሻ በማድረግ በሙያተኞች ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ጠንከር ያለ ግብረ መልስ እንደሚሰጥ ጭምር አቶ ሲሳይ አስታውቀዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ “የችግኞች የፅድቀት ምጣኔ ላይ ከወትሮው በተለየ አግባብ ለመስራት የታቀደ መሆኑን ተከትሎ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የሚሰጡ ባለሙያዎች ሳይት ድረስ እየሄዱ ቴክኒካል ድጋፍ ያደርጋሉ። ከዚህ በተጨማሪም ከስራችን ጋር በቀጥታ የሚገናኙ የትምህርት ዘርፍ ስልጠናዎችን ለማህበራት፣ ለግለሰቦች ብሎም ለተቋማት ይሰጣል፡፡ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተዛማጅነት ያላቸው በመሆኑ የምርጥ ዘር ምርጫችን ምን መሆን እንዳለበት፣ ችግኞችን እንዴት ማፍላት እንደምንችል፣ የችግኝ አተካከል ቅደም ተከተል ሂደቶችን እንዲሁም የቦታ አጠቃቀም ምን መሆን እንዳለበት ሳይንሳዊ አሰራርን በተከተለ አግባብ ማህበረሰቡ ዘላቂነት ያለው ስራ እንዲሰራ በትኩረት የምንከታተለው ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡

አዲስ አበባን በማስተር ፕላኑ መሰረት አረንጓዴ የማድረጉ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አቶ ሲሳይ፣ ተቋማት ብሎም ግለሰቦች የተከሏቸውን ችግኞች የመኮትኮት፣ የማረም ብሎም አስፈላጊውን እንክብካቤ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ችግኞቹም በእንስሳት እንዳይጠፋ እንዲሁም በግለሰቦች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከደንብ ማስከበር ጋር በመሆን የደንብ ጥሰቱን ለመከላከል እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review