ለአትሌቲክሱ ፍትሐዊነት የቴክኖሎጂ ሚና

You are currently viewing ለአትሌቲክሱ ፍትሐዊነት የቴክኖሎጂ ሚና

የአትሌቲክስ ስፖርትን ጨምሮ በየትኛውም ስፖርታዊ ውድድር ፍትሐዊነት ዋነኛው ምሰሶ ነው። የሰው ዐይን ብቻውን ሊያየው የማይችለውን ትንሹን ቅጽበት፣ የጥቂት ሚሊ ሜትር ርቀትንና የውድድሩን ህግጋት መጣስ በትክክል ለመለየትና ፍትሐዊነትን ለማስፈን ደግሞ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። በስፖርት ውስጥ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከቀላል የሰዓት መለኪያ መሣሪያዎች ተጀምሮ ዛሬ ባለው ውስብስብ የዲጂታል ዘመን የውድድሩ ዋነኛ አካል ሆኗል።

ምንም እንኳን ቴክኖሎጂዎች የሰውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ባይተኩም የቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ መዋል የውድድሮችን ፍትሐዊነት ከፍ ከማድረጉም በላይ የአትሌቶችን አፈጻጸም ለመተንተን እና ለማሻሻል እየተሰጡት ያለው ጥቅም ቀላል አለመሆኑን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያሳያል፡፡ እንደዚሁም አሰልጣኞች እና አትሌቶች በውድድሩ ወቅት ስህተቶቻቸውን በመመልከት አፈጻጸማቸውን ለማስተካከል ይረዳቸዋል።

በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ በጣም ቀላልና መሰረታዊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን አገልግሎት ላይ ማዋል ከተጀመረ ከአንድ መቶ ዓመት በላይ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። በስፖርት ውስጥ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች መካከል የሩጫ ሰዓቶች፣ ፎቶ ፊኒሽ (Photo-Finish) እና ኤሌክትሮኒክ የውጤት ሰሌዳዎች (Electronic Scoreboards) በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

የውድድሩን ፍፃሜ በትክክል ለመለየት በ1881 በፈረስ እሽቅድምድም ላይ የመጀመሪያው ፎቶ ፊኒሽ ቴክኖሎጂ እንደተሞከረ መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚያ በኋላም በተለይ በአጭር ርቀት ሩጫዎች ላይ የፍጻሜውን መስመር ማን እንደቀደመ ለመለየት ጥቅም ላይ ውሏል። እ.ኤ.አ በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ የ400 ሜትር የሴቶች ሩጫ ላይ አሊሰን ፊሊክስ እና ሻውኔ ሚለር በፍጻሜው መስመር ላይ በደረሱበት ቅጽበት አሸናፊውን ለመለየት የተቻለው ፎቶ ፊኒሽ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ነበር፡፡ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ እንደዚሁ እ.ኤ.አ በ1912 ስቶክሆልም ኦሎምፒክ ላይ በ1 ሺህ 500 ሜትር ሩጫ ላይ ኤሌክትሮኒክ የውጤት ሰሌዳዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

ከእነዚህ የመጀመሪያ እርምጃዎች በኋላ ቴክኖሎጂ በየጊዜው እያደገ መጥቶ እ.ኤ.አ በ1963 ለመጀመሪያ ጊዜ የቴሌቪዥን በቅጽበት ዳግም ማሳያ (Instant Replay) ተጀመረ። በ1970ዎቹ ደግሞ የልብ ምት መለኪያ እና ሌሎች የአትሌቶች እንቅስቃሴን የሚከታተሉ ቴክኖሎጂዎች ለስልጠና መዋል ጀመሩ። አሁን ላይ ግልጋሎት እየሰጡ ያሉት የጂፒኤስ መከታተያዎች፣ የቪዲዮ ዳኛ (VAR) እና ሌሎች ውስብስብ ቴክኖሎጂዎችም የዚያ ሂደት ውጤቶች ስለመሆናቸው ከአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ (IAAF) ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት የውድድር መጀመሪያ ላይ የተሳሳተ ጅማሬ (false start) መሆኑን የሚወስኑት የሰው ዳኞች ብቻ ነበሩ። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ምላሽ ከ0 ነጥብ 100 ሰከንድ በታች ሊሆን ስለማይችል፣ አንድ አትሌት በዚያ ፍጥነት ከተነሳ የሰው ዳኛ ለመወሰን ይቸገራል። ዘመናዊው የኤሌክትሮኒክስ ዳሳሽ (Electronic Sensor) ቴክኖሎጂ ግን ይህንን ስህተት አርሟል። ይህ ቴክኖሎጂ አትሌቱ በጀማሪው ብሎክ ላይ የፈጠረውን ኃይል የሚለካ ሲሆን፣ ጥይቱ ከመተኮሱ በፊት የሚፈጠር ማንኛውም እንቅስቃሴ በቅጽበት ይለያል። በዚህም ምክንያት የውሸት ጅማሬ ለመፈጸም ከ0 ነጥብ 100 ሰከንድ ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተነሳ አትሌት ቴክኖሎጂው በማሳወቁ ከውድድር ሊሰረዝ ይችላል። በዚህ መንገድ የቴክኖሎጂው መረጃ በሰው ዳኞች ሊፈጠር ይችል የነበረውን ስህተት አርሞ ፍትሐዊነትን ያረጋግጣል።

በቅርቡ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ፍትሐዊነትን ለማሳደግ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ተስፋ ተጥሎባቸዋል። የካሜራ ዳሳሾች (Cameras and Sensors) አንዱ ሲሆን፣ ውድድሩን ከሁሉም አቅጣጫ ለመቅረጽ የሚያስችሉ ካሜራዎች እየበዙ ይገኛሉ። ይህም ዳኞችን በውድድሩ ወቅት ለሚፈጠሩ ጥቃቅን ውሳኔዎች ለመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትና በከፍተኛ ዝላይ (High Jump) እና የረዥም ዝላይ (Long Jump) ውድድሮች ላይ የአትሌቱን አፈጻጸም በትክክል ለመለየት ያገለግላል ተብሎ ይጠበቃል።

የተሻሻለ የፎቶ ፊኒሽ ቴክኖሎጂ (Improved Photo-Finish Technology) እንደዚሁ አዳዲስ የፎቶ ፊኒሽ ሲስተሞች ከበፊቱ በበለጠ ከፍተኛ ጥራት ባለው ፍሬም ሩጫዎችን ለመመዝገብ ይችላሉ። ይህ በቅጽበት የተሻሉ ምስሎችን በመያዝ ትክክለኛ ውጤት ለመስጠት ይረዳል ይላሉ የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ቴክኒካል ቡድን አባሉ አይ ጉዬ።

በእርግጥ በአትሌቲክስ ውድድሮች ወቅት አወዳዳሪው አካል ብቻ ሳይሆን አትሌቶችም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ በአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ አትሌቶች የሚጠቀሟቸው ቴክኖሎጂዎች በዋነኛነት ለስልጠና እና ለአፈፃፀም ብቃት ማሻሻያ የሚያገለግሉ ሲሆን፣ በውድድሩ ወቅት ደግሞ የውድድሩን ህግጋት ከጠበቁ ቴክኖሎጂዎች ብቻ ይጠቀማሉ።

አትሌቶች ስማርት ሰዓቶችና የመከታተያ መሳሪያዎችን (Fitness Trackers and GPS Watches) ተጠቅመው የአትሌቱን የልብ ምት፣ የሩጫ ፍጥነት፣ የተጓዘበትን ርቀት፣ የእንቅልፍ ጥራት እና ሌሎች የጤና መረጃዎችን ይመዘግባሉ። ይህ መረጃ አሰልጣኞች ለአትሌቱ ትክክለኛውን የስልጠና መርሃ ግብር እንዲያዘጋጁና የድካም ደረጃውን እንዲገመግሙ ይረዳቸዋል።

አትሌቶች የሩጫ ቴክኒካቸውን፣ የዝላይ አቀማመጣቸውን ወይም የውርወራ እንቅስቃሴያቸውን በዝግታ በመመልከት ስህተቶቻቸውን በቀላሉ ለማረም የሚረዳው ሌላኛው ቴክኖሎጂ የቪዲዮና የ3ዲ እንቅስቃሴ ትንተና ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ የአካል ክፍሎች እንቅስቃሴን ከሁሉም አቅጣጫ ስለሚቀርጽ፣ አትሌቶች ትክክለኛውን እንቅስቃሴ በመማር የአፈጻጸም ብቃታቸውን ከፍ ያደርጋሉ።

አንዳንድ አትሌቶች በስልጠና ወቅት ሰውነታቸው ኦክሲጅንን እንዴት እንደሚጠቀም ለመረዳት የመተንፈሻ መሳሪያዎች ይጠቀማሉ። ይህም የመተንፈስ ችሎታቸውን ከፍ ለማድረግ እና በውድድር ወቅት ድካምን ለመቋቋም ይረዳቸዋል።

በውድድር ህጎች መሰረት አትሌቶች የሚፈቀድላቸውን ቴክኖሎጂዎች ብቻ መጠቀም ይችላሉ። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ እና የውድድሩን ህግጋት ለመጠበቅ ወሳኝ ናቸው። በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ህግ መሰረት የተሰሩ የስፖርት ጫማዎች ይፈቀዳሉ። እነዚህ ጫማዎች በአብዛኛው ከካርቦን ፋይበር የተሰሩና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ሊኖራቸው ይችላል። ይሁንና የጫማው ውፍረት እና የሰሌዳው አይነት በህግ ቁጥጥር ስር ናቸው። በተለይም በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተሰሩት ዘመናዊ ጫማዎች፣ ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተለየ መልኩ የአትሌቶችን አፈጻጸም በእጅጉ የሚያሻሽሉ መሆናቸው ተረጋግጧል። ይህ ቴክኖሎጂ አትሌቶች ክብረ ወሰን እንዲሰብርና ፈጣን ሰዓቶችን እንዲያስመዘግቡ በመርዳት ላይ ይገኛል።

የቴክኖሎጂው እድገት አትሌቲክስን የበለጠ ፍትሐዊ ለማድረግ ለዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን (World Athletics) ፈተና ሆኖበታል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ አትሌቶች የሚለብሷቸውን ጫማዎች በተመለከተ የሚከተሉትን ህጎች አውጥቷል። ለየሩጫው ርቀት የጫማው ውፍረት ከፍተኛ ገደብ ተጥሎበታል። ለምሳሌ፣ ለጎዳና ላይ ውድድሮች (ማራቶን) የጫማው ሶል ውፍረት ከ40 ሚሊ ሜትር መብለጥ የለበትም። ለትራክ ውድድሮች ደግሞ ውፍረቱ ከ20 እስከ 25 ሚሊ ሜትር መብለጥ የለበትም።

በመጪው በቶኪዮ 2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከላይ ከተገለፁት በተጨማሪ በርካታ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ የሚድጉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ዋነኞቹ የውድድሩን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ እና ለተመልካች የተሻለ የውድድር ልምድ ለማቅረብ የሚውሉ ናቸው። የሻምፒዮናው ይፋዊ ቴክኖሎጂ አጋር የሆነው ሶኒ (Sony) እና ሌሎች አጋሮች በመተባበር የሚያቀርቧቸውን ቴክኖሎጂዎች በዝርዝር እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።

ሃውክ-አይ ኢኖቬሽን የሶኒ ንዑስ ኩባንያ ሲሆን፣ የቪዲዮ ዳኝነት ስርዓቱን በሁሉም የትራክ እና የሜዳ ውድድሮች ላይ ይዘረጋል። ይህ ሲስተም ለዳኞች ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ የቪዲዮ ምስሎችን በማሳየት ፍትሐዊ እና ትክክለኛ ውሳኔ እንዲሰጡ ይረዳል። ለምሳሌ ያህል፣ በዝላይ ውድድሮች ላይ የአትሌቱን አፈጻጸም፣ በሩጫ ውድድሮች ላይ ደግሞ የውሸት ጅማሬ (False Start) መኖሩን ለመወሰን ያግዛል ተብሎለታል።

የሻምፒዮናው ቀረጻ የሚካሄደው አልፋ (Alpha™) በተሰኙ መስታወት አልባ ካሜራዎች እና ጂ ማስተር (G Master™) ሌንሶች ነው። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የአትሌቶችን እንቅስቃሴ በሲኒማ ጥራት ለመቅረጽ እና በቅጽበት ለስርጭት ለማቅረብ ያስችላሉ። ይህም የአትሌቶቹን ድንቅ እንቅስቃሴዎች በቅርበት እና በግልጽ እንዲያዩ ይረዳል የተባለው ቴክኖሎጂ በተግባር ላይ እንደሚውል ተገልጧል።

በአጠቃላይ የአትሌቶች የመሮጫ ጫማ ቴክኖሎጂ ፍጥነትን እና ብቃትን በማሳደግ በስፖርቱ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ሆኖም የፌዴሬሽኑ ህጎች ይህ ቴክኖሎጂ ከአትሌቱ የራሱ ተሰጥኦና ጥረት በላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ለመቆጣጠር ይረዳሉ።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review