ፕሮጀክቶችን በጥራት እና በፍጥነት በማጠናቀቅ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውበ በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች መሰራታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነቸ አበቤ ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ የተገነቡ የተላየዩ መሰረተ ልማቶች እና ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ከንቲባ አዳነች አበቤ እና የተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎቸ በተገኙበት በትናንትናው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል፡፡
በመርሐ-ግብሩም አዲስ አበባ ከተማ ለዓመታት ተጫጭኗት ከነበረው እርጅና እና ድካም እንድትወጣ በርካታ አሥርት ዓመታት መሻገሯን ከንቲባ አዳነች አመላክተዋል፡፡
መንግስት ከለውጡ በፊት አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እና ውብ ለማድረግ እንዲሁም ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለጎብኝዎች ሳቢ እና ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን በተገባው ቃል መሰረት በአጭር ጊዜ ባለፉት ስድስት ዓመታተ ብቻ በዓይን የሚታይ ስራ በተግባር እውን ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ በከተማዋ በየቀኑ አዳዲስ ፕሮክጀቶች ማስመረቅ መደበኛ ስራ እየሆነ መጥቷል ያሉት ከንቲባዋ፣ በ2017 ዓ.ም 19 ሺህ የሚጠጉ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መመረቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
ተመርቀው ለአገልገሎት ከፍት የሆኑት ፕሮጀክቶች የተሰሩባቸው አካባቢዎች ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ በምታካሂድበት ወቅት የነበራቸው ገፅታ ጥሩ ስላልነበር በቆርቆሮ እና በባነር በመከለል ገመናችንን ስንሸፍንባቸው የነበሩ ቦታዎች ናቸው ሲሉ ከንቲባዋ ተናገረዋል፡፡

አሁን ላይ እነዚህን አካባቢዎች በማልማት ለትራፊክ መሳለጥ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባሻገር ልዩ ውበትን በማጎናፀፍ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ከመፍጠር ባለፈ የስራ ዕድል ምንጭ እንዲሆኑ የሚያስችል ስራ መሰራቱንም ገልፀዋል፡፡
ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል ከሜክሲኮ እስከ ለገሃር ባለው ቦታ ብቻ 2 ሺህ 145 የሚጠጋ መኪናን ማስተናገድ የሚቸሉ 13 ፓርኪንግ እና ወደ 1 ሺህ 624 የሚደርሱ ታክሲና አውቶብስ ማስተናገድ የሚችሉ 10 የሚደርሱ ተርሚናሎች ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ፕሮጀክቶቹ 300 የሚሆኑ ሱቆች የያዙ ሲሆን፣ ለሬስቶራንት እና አንፊ ቲያትር እንዲሁም ኢግዚብሽኖችን ለማዘጋጀት እንዲረዳ ሆነው የተዘጋጁ ፕላዛዎች ያካተቱ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም ትንንሽ ነገሮች ተጀምረው የማይጠናቀቁበት ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩ የግንባታ ጅምሮች የነበሩበት ሁኔታ የተቀየረበት እንዲሁም ቆሽሸው ጠረናቸው የሚከረፋ የነበሩ አካባቢዎች አሁን ላይ በ24/7 የስራ ባህል አዳዲስ ፕሮከጅቶችን በአጭር ጊዜ በፍጥነት እና በጥራት በማከናወን ለከተማው ነዋሪ አዳዲስ በስራት እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በኢትዮጵያ ማንሰራራት ሂደት ውስጥ አዲስ አበባ የብልፅግና ተምሳሌት የሆነ ስራ በመስራት ከተማዋ የልምድ መቅሰሚያ ማዕከል መሆኗን ነው ከንቲባዋ የገለፁት፡፡
በከተማዋ በለውጡ ማግስት የተጀመረው የዕድገት ጉዞ፣ በየዓመቱ ደረጃውን ጠብቆ በፍጥነት፣ በጥራት እንዲሁም በብዛት እየጨመረ መምጣቱን ያነሱት ከንቲባዋ፣ በተሰሩ ስራዎች ከተማዋ ክብራችንን የሚመጥን እና የምንኮራባት እየሆነች ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መልክ መሆኗን በማንሳትም፣ የአዲስ አበባ መበልፀግ እና በፍጥነት ማደግ እና ፕሮጀክቶችን በፈጠራና በፍጥነት ማጠናቀቅ ለሀገራችን ትልቅ መነቃቃት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አሁን ላይ በመላው ሀገራችን ተስፋፍቶ በ70 ከተሞች እየተተገበረ ሲሆን፣ ይህም ደረጃቸውን የጠበቁ ለመኖር ምቹ የሆኑ ከተሞች እየተፈጠሩ ነው ብለዋል፡፡
በያለው ጌታነህ