በጃፓን ዮኮሃማ ከተማ ከተካሄደው የTICAD 9 የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በትናንትናው ዕለት በጃፓን የኢፌዲሪ ኤምባሲ አዘጋጅነት የኢትዮ-ጃፓን የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሂዷል።
በፎረሙ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከ100 በላይ የሚሆኑ በዋናነት ከጃፓን እና ከኢትዮጵያ የተውጣጡ የኩባንያ ባለቤቶች እና ስራ አስኪያጆች ተሳትፈዋል።
በጃፓን በተካሄደው የTICAD-9 የመሪዎች ጉባዔ የሚሳተፈውን የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን የመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ባደረጉት ንግግር፣ የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችና ቢዝነስ አማራጮች እንዲሰማሩና ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ በበኩላቸው፣ ሀገራችን ባላት ስትራቴጅካዊ አቀማመጥ፣ ወጣትና የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ጠንካራ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ጋር ተዳምሮ ተመራጭ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ማስቻሉን መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በጃፓን የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዳባ ደበሌ፣ የሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር በኤምባሲው በኩል ሰፊ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ የተካሄደው ፎረምም የዚህ ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል።