ማንችስተር ዩናይትድ የመጀመሪያ ድል ለማግኘት ፉልሃምን ይገጥማል

You are currently viewing ማንችስተር ዩናይትድ የመጀመሪያ ድል ለማግኘት ፉልሃምን ይገጥማል

AMN – ነሃሴ 18/2017 ዓ.ም

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት መርሃግብር ዛሬም ሲቀጥል ሦስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።

ክሪስታል ፓላስ በሜዳው ሰልኸረስት ፓርክ ኖቲንግሃም ፎረስትን ይገጥማል። ኤቤሬቺ ኤዜን ለአርሰናል የሸጠው ፓላስ በመጀመሪያ ሳምንት ከቼልሲ ጋር አቻ መለያየቱ ይታወሳል።

ከክለቡ ባሌቤት ጋር ግጭት ውስጥ የገቡት የኖቲንግሃም አሰልጣኝ ኑኖ ስፕሪቶ ሳንቶ የሊጉ የመጀመሪያው ተሰናባች አሰልጣኝ ሊሆኑ ይችላሉ።

ብሬንትፎርድን በማሸነፍ የውድድር ዓመታቸውን በድል የጀመሩት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ዛሬ ከፓላስ ትልቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

በተመሳሳይ 10 ሰዓት ኤቨርተን ብራይተንን ያስተናግዳል። ጉዲሰን ፓርክን የተሰናበተው የመርሲሳይዱ ክለብ በአዲሱ ስታዲየሙ ሂል ዲክሰን የመጀመሪያ የፉክክር ጨዋታውን ያደርጋል።

ሁለቱም ክለቦች በመጀመሪያ ሳምንት መርሃግብራቸው ድል አልቀናቸውም።

ኤቨርተን በሊድስ ዩናይትድ ሲሸነፍ ፣ ብራይተን ከፉልሃም ጋር አቻ ተለያይቷል።

ምሽት 12:30 የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ በክራቫን ኮቴጅ ይከናወናል።

በአርሰናል ተሸንፎ የጀመረው ማንችስተር ዩናይትድ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለማስመዝገብ ወደ ምዕራብ ለንደን አቅንቷል።

በዩናይትድ በኩል ግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና ወደ ስብስቡ ሲመለስ ራስመስ ሆይሉንድ አብሮ አልተጓዘም።

በአንፃሩ አጥቂው ቤንጃሚን ሼሽኮ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ኑሲየር ማዝራዊ እና ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው።

በአርሰናሉ ጨዋታ ጥሩ ብቃት እንዳሳየ የተነገረለት ዩናይትድ በክራቫን ኮቴጅ ጥሩ ክብረወሰን አለው። ዛሬ ድል ከቀናው ለዘጠነኛ ተከታታይ ጊዜ ይሆናል።

ዩናይትድ መሻሻሉን ለማሳየት ጨዋታውን በድል ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል። በተለይ አሰልጣኙ ሩበን አሞሪም በሊጉ ያለውን ደካማ ክብረወሰን ማሻሻል ካልቻለ ጫና ውስጥ መግባቱ አይቀርም።

የ40 ዓመቱ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ቀያይ ሰይጣናቱን በመራባቸው 28 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በ15ቱ ተሸንፏል። ማሸነፍ የቻለው ሰባቱን ብቻ ነው።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review