የምክር ቤት አባላት በህዝብና መንግስት መካከል መዳደላድልን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር ገለፁ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለአመራርና አባላቱ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር፤ የምክር ቤት አባላት በባለፈው በጀት አመት በሀሳብና በተግባር ወደ ህዝቡ በመቅረብ በህዝብና መንግስት መካከል መዳደላድልን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በአሰራር፣ በሰው ሀይልና በቴክኖሎጂ እራሱን በማደራጀት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ያነሱት ዋና አፈ-ጉባኤዋ በዚህም በባለፈው በጀት አመት ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
የመጡ ውጤቶችን ለማስቀጠል የምክር ቤት አባላቱ በሁለንተናዊ መልኩ የበቁ ብሎም ተልዕኮዎችን በስኬታማነት መወጣት እንዲችሉ ማድረግ ቁልፍ ተግባር መሆኑን ያነሱት ዋና አፈ ጉባኤዋ፤ ለዚህም የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች አስፈላጊ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው የሀገሪቱን እና የከተማዋን ራእይ ለመሳካት፤ ብሎም በማስፈፅም ተግባራት የሚገጥሙ ችግሮችን በብቃት ለመወጣት የሚያግዝ ስለመሆኑም አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር ተናግረዋል።
ለምክር ቤት አመራርና አባላቱ የሚሰጠው ስልጠና ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑም ተመላክቷል።
በራሄል አበበ