በማቻከል ወረዳ በጎርፍ የተወሰደውን የጌደብ ወንዝ ድልድይ በተገጣጣሚ ብረት በመገንባት ለተሽከርካሪ ክፍት ማድረጉን የወረዳው መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የወረዳው መንገድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ የስጋት ግዛቸው ለኢዜአ እንደገለጹት ድልድዩ ነሐሴ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በጮቄ ተራራ ላይ የጣለው ዝናብ በፈጠረው ከፍተኛ ጎርፍ ጉዳት ደርሶበታል።
በድልድዩ መወሰድም ከደብረ ማርቆስ ወደ ባህርዳርና ሌሎች ወረዳዎች ይደረግ የነበረው የሰውና የተሽከርካሪ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ መቆየቱን ገልጸዋል።
ይህም በአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ እንደነበር አውስተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የደብረማርቆስ መንገድ ጥገና ዲስትሪክት እና የዞኑ አስተዳደር ባደረጉት ርብርብ ድልድዩን በተገጣጣሚ ብረት መልሶ በመገንባት ለእግረኞች ክፍት መደረጉ መዘገቡ ይታወሳል።
ቀደም ሲል ለእግረኞች ክፍት የተደረገው መንገድ በዛሬው እለት ደግሞ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ መጀመሩን ገልጸዋል።
ድልድዩ ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ሲጠባበቁ ለቆዩ መንገደኞችና አሽከርካሪዎች ላሳዩት ትእግስት አቶ የስጋት ምስጋና ማቅረባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
በጎርፍ የተወሰደውን ድልድይ በአጭር ጊዜ መልሶ በመገንባት ለህብረተሰቡና ለተሽከርካሪ አገልግሎት እንዲሰጥ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።