በአዲስ አበባ የተገነቡ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች እና ተርሚናሎች ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ማስቀረት መቻላቸውን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ዘርጋው ገለፁ፡፡
ከ ሁለት ያልዘለለ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ብቻ የነበሩባት የአዲስ አበባ ከተማ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለቁጥር የበዙ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎችን እና ተርሚናሎችን መገንባት ችላለች፡፡
በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ ከ150 በላይ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚዎች እና ከ40 በላይ ተርሚናሎች ተገንብተዋል፡፡
በዚህም ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ማስቀረት መቻሉን ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ዘርጋው ተናግረዋል፡፡

መሠረተ ልማቶቹ ዝናብና ፀሀይን የሚከላከሉ፣ ማረፊያ ስፍራ ያላቸው እና የደህንነት ካሜራም የተገጠመላቸው በመሆኑ መዲናዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በቂ የማቆሚያ ስፍራ ስላልነበረ በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ ለረጅም ጊዜ በመቆም በትራፊክ ፍሰቱ ላይ መስተጓጎል ይፈጠር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ሥራው ከኮሪደር ልማት ጋር ተዳምሮ ከተማዋን ለሁሉም አይነት ዜጋ ምቹ እና ተስማሚ አድርጓል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
በከተማዋ በሁሉም ዘርፍ የሚካሄደው ልማት አዲስ አበባ ወደ ተሟላ የከተሜነት ደረጃ የሚያሸጋግራት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በማሬ ቃጦ