እንግሊዛዊቷ ኢቴል ካተርሃም ሚያዝያ 30 ነበር በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ የዓለማችን የዕድሜ በለጸጋ በሚል ዕውቅና ያገኘችው፡፡
ስሟ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ መስፈር የቻለው ብራዚላዊቷ ኢናህ ካናባሮ ሉካስ በ116 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷን ተከትሎ ነው፡፡
ኢቴል ካተርሃም ባለፈው ሀሙስ እለት ነበር ከቤተሰብ ጋር ሆና የልደት ቀናን በድምቀት ያከበረችው፡፡
ኢቴል ካተርሃም፣ ግላዲስ ባቢላ የተባለች አህት ነበረቻት፡፡ ግላዲስ ባቢላ የዛሬ 23 ዓመት ገደማ በፈረንጆቹ 2002 ላይ በ104 ዓመት ከ78 ቀን ህይወቷ ማለፉን የዩ ፒ አይ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ካተርሃም በህይወት ዘመኗም ሁለት ሴት ልጆች (በህይወት የሌሉ)፣ 3 የልጅ ልጆች እና 5 የልጅ ልጅ ልጆች ማፍራት ችላለች፡፡
116ኛ የልደት በዓል ባከበረችበት ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን ቃለ መጠይቅ ለመስጠት አለመፈለጓ በቃል ዓቀባይ በኩል ተገልጿል፡፡ ይህን ማድረግ የፈለገችው ከቤተሰቦቿ ጋር ጊዜ ማሳለፈ ፈልጋ ነው ተብሏል፡፡
ይሁንና የዩናትድ ኪንግደም ንጉስ ቻርለስ ጥሪ የሚያደርጉላት ከሆነ ሀሳቧን ልትቀይር ትችላለች፡፡
ረጅም ዕድሜ የመኖሯ ሚስጥር ምን ይሆን ተብሎ በአንድ ወቅት ለቀረበላት ጥያቄም “ለእያንዳንዱ አጋጣሚ “አዎ” የሚል ምላሽ ስጥ፤ ምክንያቱም ወዴት እንደሚያመራ አታውቅምና” ስትል ተናግራለች፡፡
አዎንታዊ አመለካከት እና ሁሉንም ነገር በልክ ማድረግም ጠቃሚ የህይወት መርህ ሊሆኑ እንደሚገባም ካተርሃም ገልፃ ነበር፡፡
በማሬ ቃጦ