ለመንግስት ሰራተኞች ከተደረገዉ የደሞዝ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነዉ

You are currently viewing ለመንግስት ሰራተኞች ከተደረገዉ የደሞዝ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነዉ

AMN- ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም

ለመንግስት ሰራተኞች ከተደረገዉ የደሞዝ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ተናገሩ።

አዲስ አመትን ጨምሮ በቀጣይ በሚከበሩ በዓላት የተረጋጋ ግብይት እንዲኖርና የኑሮ ውድነትን ለማቅለል የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ እንዲሁም የገበያ ማረጋጋት ህገ ወጥ ንግድ ቁጥጥርና የኢትዮጽያ አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ግብረ ሃይል ሰብሳቢው አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የምርት አቅርቦትን በማሳደግ የኑሮ ውድነት ጫናን የማቅለል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

መዲናዋ የገበያ አማራጮችን በማስፋት የምርት አቅርቦትን በማሳደግ የተረጋጋ ግብይት እንዲፈጠር ማድረግ መቻሉንም አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል።

በ5 የገበያ ማዕከላት፣ በሰንበት ገበያዎችና በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት አምራቾች በቀጥታ ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና እያቃለሉ መሆናቸውንም አቶ ጃንጥራር አንስተዋል።

በኑሮ ውድነቱ ጫና ሊደርሰባቸው የሚችሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መዲናዋ 14.5 ቢሊየን ብር በመደጎም እየተሰራ መሆኑንም ነው አቶ ጃንጥራር የገለጹት።

ህገ ወጥ ግብይትና የዋጋ ጭማሪ እንዳይፈጠርም ግብረ ሃይሉ በየጊዜው ክትትል በማድረግ አበረታች ውጤት መመዝገቡንም ገልጸዋል።

ድጎማውም ለተማሪዎች ምገባ፣ ለትራንስፖርትና የኑሮ ጫናን ማቅለል በሚችሉ ዘርፎች የተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ለመንግስት ሰራተኞች ከተደረገዉ የደሞዝ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖርም ግብረ ሃይሉ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግም አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል።

በቴዎድሮስ ይሳ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review