የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ውስጣዊ አንድነትንና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)ገለፁ።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽ(አሚኮ) 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ “መገናኛ ብዙሃን ለብሄራዊ ጥቅምና ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ አውደ ጥናት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ” ሚዲያ ለብሔራዊ ጥቅም” በሚል ርዕስ በአውደ ጥናት ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በዚህ ጽሁፋቸው እንዳመለከቱት፥ መላው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሁለንተናዊ መንገድ ለማስከበር በአንድነት ሊረባረብ ይገባል።
የሀገሪቱን ብሔሄራዊ ጥቅም የሚጎዳ ማንኛውንም እንቅስቃሴ በሀሳብ የበላይነት መሞገትና ማክሸፍም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለዚህም ውስጣዊ እንድነትና ሰላምን በማስጠበቅ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አቅምን ማጠናከርና የዴሞክራሲ አቅም በመገንባት መረባረብ እንደሚገባ አብራርተዋል።
መንግስት የኢትዮጵያን ብልፅግና በሁለንተናዊ መንገድ ለማረጋገጥ በሁሉም መስክ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በመሆኑም መገናኛ ብዙሀን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ላይ አጀንዳ ፈጥረው መስራት እንዳለባቸው ማሳሰባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአውደ ጥናቱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤን ጨምሮ ሌሎቸም የስራ ሀላፊዎች እየተሳተፉ ሲሆን፤ በቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።