የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ከቼክ ብሔራዊ ሙዚየም እና ከቼክ ዲቨሎፕመንት ኤጀንሲ ሀላፊዎች ጋር ስምምነቱን በፕራግ ከተማ በዛሬው እለት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ ህፃናትን ማእከል ያደረገ ዘመናዊ ሙዚየም መገንባት የሚያስችል ሲሆን፣ የቼክ ሪፐብሊክ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተነግሯል::
ይህ ቋሚ የልጆች ሙዚየም በወዳጅነት ቁ.2 ፓርክ ውስጥ እንደሚገነባም ሚኒስቴሩ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በላከው መረጃ ገልጿል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የህፃናት ሙዚየሙ ህፃናት ቀለል ባለ መንገድ ስለ ሀገራቸው ታሪክ እና ባህል እውቀት እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በላይ በፈጠራ፣ በትምህርትና በእውቀት እንዲጎለብቱ እድል የሚፈጥርላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
የቼክ መንግስት ይህንን ሙዚየም ለማቋቋም ለሚያደርገው የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል::
ይህ ቋሚ የህፃናት ሙዚየም ፕሮጀክት ህፃናት የቱሪዝም ሀብቶቻቸውን አውቀው እንዲያድጉ እና በዘርፉ ልማት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚያግዝ እንደሆነም ተገልጿል፡፡