የእስራኤል አስተዳደር በሃማስ እጅ የሚገኙ ታጋቾችን ሙሉ ለሙሉ ለማስለቀቅ የቀረበውን የስምምነት ሀሳብ እንዲቀበል የሀገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ ጠይቀዋል።
የጦር አዛዡ ሌተናል ጀነራል ኢያል ዛሚር “የእስራኤል ጦር በውጊያ ባስመዘገበው ድል ለስምምነት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን መፍጠር ችሏል” ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
“አሁን ሁኔታዎች ያሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እጅ ላይ ነው” ያሉት አዛዡ፣ ሁሉም ታጋቾች በሚመለሱበት ሀሳብ ላይ መስማማት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በነገው ዕለት በቀጣናው አደራዳሪዎች በቀረበው እና ሃማስ ከሳምንት በፊት በተስማማበት የተኩስ አቁም ስምምነት ዙሪያ የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።
ካቢኔው ስብሰባውን የሚያደርገው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ጦርነቱ እንዲቆም እና ታጋቾች እንዲመለሱ በቴልአቪቭ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደሆነም ተገልጿል።
በነገው ዕለት የታጋች ቤተሰቦች ፎርም የተባለው ማህበር ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ማቀዱም ተሰምቷል።
የእስራኤል ጦር አዛዥ ሌተናል ጀነራል ኢያል ዛሚር በአሁኑ ወቅት በርካታ እስራኤላውያን የሚፈልጉት የታጋቾችን መለቀቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሁለቱን ተዋጊ ወገኖች በማደራደር ላይ የሚገኙት ግብፅ እና ኳታር የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ በሁለት ዙር ቀሪ ታጋቾች ሙሉ ለሙሉ እንዲለቀቁ ሀሳብ አቅርበዋል።
በሃማስ እና በአሜሪካ ተቀባይነት ባገኘው በዚህ ሀሳብ በ60 ቀናት ውስጥ ጦርነቱ በዘላቂነት በሚገታበት ሁኔታ ላይ ድርድር እንዲደረግም ይጠይቃል።
አሁናዊ ቁጥራዊ መረጃዎችም 1.9 ሚሊየን (90 በመቶ) የጋዛ ነዋሪዎች ከቀያቸው ሲፈናቀሉ፣ 500 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ለከፋ ርሀብ መጋለጣቸውን፤ ከ62 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን ይጠቁማሉ።
በዳዊት በሪሁን