በመዲናዋ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

You are currently viewing በመዲናዋ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN – ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም

የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ።

የሀሰተኛ ሰነዶች ዝግጅት ወንጀል በሀገር ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነና ፖሊስም በዚህ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችን በተለያዩ ጊዜያት በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እያቀረበም እንደሚገኝ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ፣ በክፍለ ከተማው ወረዳ 11 ልዩ ቦታው አጃምባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሀሰተኛ ሰነዶችን በሚያዘጋጁ ግለሰቦች ላይ ጥናትና ክትትል ሲያደረግ መቆየቱ ተገልጿል።

ነሐሴ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሠዓት አካባቢ በተጠቀሰው ቦታ የሚገኝና፣ ፖሊስ በጥናት የደረሰበትን የተጠርጣሪ ሰይፈዲን ሼህቦ መኖሪያ ቤት ላይ የፍርድ ቤት የመበርበሪያና የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣት ፍተሻ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡

ባደረገው ፍተሻና ብርበራም የተለያዩ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የቀበሌ መታወቂያ፣ የንግድ ፈቃድ፣ የምስክር ወረቀት፣ የተለያዩ የወሳኝ ኩነት ሰርተፍኬቶች፣ መንጃ ፈቃድ፣ የእጅ በእጅ ደረሰኞች፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲሁም ሀሰተኛ ሰነዶቹን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙባቸው 2 ላፕቶፕ፣ 3 ማተሚያ ማሽን ( ፕሪንተር ) እና የተለያዩ ቀለሞች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተመላክቷል፡፡

በዚህም ከዋና ወንጀል አድራጊው ሰይፈዲን ሼህቦ በተጨማሪ፣ በአባሪነት ተሳትፎ ያደረገውን አብይ አያሌው የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፣ ፖሊስ የተያዙ ሰነዶችን የማረጋገጥ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ የማስፋት ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠል ክስ እንደሚያስመሰርት ገልጿል፡፡

ህብረተሰቡ ሀሰተኛ ሰነዶችን መገልገል በህግ ሊያስጠይቅ የሚችል ወንጀል መሆኑን በመገንዘብ፣ ከመሰል ድርጊቶች ራሱን ሊያርቅ እንደሚገባም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review