ለግንባታ ሥራ ቅልጥፍና ሲባል ከነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የግንባታ ሥራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ከጀርመን አደባባይ እስከ ኃይሌ ጋርመንት ያለው የቀለበት መንገድ ክፍል በከፊል ለትራፊክ ዝግ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አካል የሆነውን የሳር ቤት – ከጀርመን አደባባይ – ለቡ – ኃይሌ ጋርመንት ኮሪደር ግንባታ በፍጥነት ለማጠናቀቅ በከፍተኛ ርብርብ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። በመሆኑም ለግንባታ ሥራው ቅልጥፍና ሲባል ከነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የግንባታ ሥራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ከጀርመን አደባባይ እስከ ኃይሌ ጋርመንት ያለው የቀለበት መንገድ ክፍል በከፊል ለትራፊክ ዝግ እንደሚደረግ አስታዉቋል።

በዚሁ መሠረት የሳር ቤት – ጀርመን አደባባይ – ለቡ – ኃይሌ ጋርመንት ኮሪደር ግንባታ ስራ እስኪጠናቀቅ ድረስ አሽከርካሪዎች:
1ኛ/ ከአየር ጤና ወደ ጋርመት እና ለቡ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች፤ በጀሞ ሚካኤል አድርጎ ወደ ፉሪ አደባባይ ጋርመት የሚወስደውን መንገድ:
2ኛ/ ከሣር ቤት መካኒሳ ወደ ጋርመንት እና ለቡ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች፤ በጀሞ ሚካኤል ወደ ፉሪ አደባባይ ጋርመት የሚወስደውን መንገድ:
3ኛ/ ከቄራ በጎፋ ወደ ጋርመት እና ለቡ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች፤ በጎፋ መብራት ኃይል ላፍቶ የሚወስደውን መንገድ:
4ኛ/ ከማሠልጠኛ እና ሠፈራ ወደ ጀሞ ሚካኤል እና አየር ጤና የሚጓዙ አሽከርካሪዎች በሀጫሉ መንገድ ወደ ፉሪ አደባባይና ጀሞ የሚወስደውን አማራጭ መንገድ በመጠቀም ለግንባታ ሥራው መፋጠን የተለመደውን ትብብር እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።