ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከመስከረም ወር 2018 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ማሻሻያ እንዲደረግ መወሰኑ ይታወቃል።
ይህንን ተከትሎ የሚደረግን ህጋዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ፣ የምርት ማሸሽ እንዲሁም የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል። የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ማማሻያ ውሳኔን መሰረት በማድረግ በምርት እና አገልግሎት ላይ ዋጋ በሚጨምሩ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድ የኢፌዴሪ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በህግ አሰራር የሚመራ የንግድ ስርዓትና የግብይት ሂደትን ያልተከተለ ያልተጋባ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ፣ ምርትን ማከማቸትና ከዝኖ ማስቀመጥ አስተዳደራዊና ህጋዊ ተጠያቂነትን ያስከትላል ሲሉም ገልፀዋል፡፡ የደሞዝ ማሻሻያን መነሻ ያደረገ የአገልግሎትና የዋጋ ጭማሪ ከግል ጥቅመኝነትና ሁኔታዎችን ካለማጤን የሚመነጭ የተሳሳተ እርምጃ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የህብረተሰቡን ስጋት የሚቀርፍ ይህንን የመከላከል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው ችግሮች ከተስተዋሉ አስተማሪ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል። የንግዱ ማህበረሰብ ለህግ ተገዥ በመሆን ሀገሩንና ወገኑን በቅንነት በታማኝነትና በኃላፊነት ስሜት ማገልገል አለበት ሲሉም ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአለኸኝ አዘነ