ለፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ትልቁ ፈተና ጉዳት ነው፡፡ የስፖርት ሕይወታቸውን ሙሉ ለሙሉ ሊቀይረው ይችላል፡፡ በቻሉት ልክ ጥንቃቄ ማድረግ ቢችሉም ከቁጥጥራቸው ውጪ ጉዳት መግጠሙ ግን አይቀርም፡፡
የጉዳት ዓይነቶቹ ብዙ እና የሚያደርሱትም ተፅእኖ የተለያየ ነው፡፡ ለስፖርተኞች ግን እንደ ኤንቴሪር ክሩሼት ሊጋሜንት ( anterior cruciate ligament (ACL) የሚያስፈራ ጉዳት የለም፡፡ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ከእንቅስቃሴ ስለሚያግድ ስፖርተኞች ኤ ሲ ኤል ሲገጠማቸው በስነ ልቦናም በእጅጉ ይጎዳሉ፡፡ ኤ ሲ ኤል የጅማት ዓይነት ሲሆን ስራው ከጉልበት በታች ያለው የሰውነት ክፍላችን (ቅልጥም) የታፋ አጥንት ወደ ፊት እንዳይንሸራተት የሚጠብቅ እንደሆነ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአጥንት ቀዶ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሰይድ ሞሐመድ ይገልፃሉ፡፡ በመጠን ከሌሎቹ ትልቅ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ጅማት በተለያየ አጋጣሚ ለጉዳት ይዳረጋል፡፡ በተለይ ስፖርተኞች የዚህ ጉዳት ሰለባ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡

ዶክተር ሰይድ እንደገለፁት ስፖርተኛው ከፈጣን እንቅስቃሴ በድንገት የሚያስቆም ሁኔታ ከገጠመው ፤ አልያም ወደ ላይ ዘሎ በሚያርፍበት ወቅት ሚዛኑን ጠብቆ ካላረፈ የኤ ሲ ኤል ጉዳት ሊገጥመው ይችላል፡፡ በተለይ የእግርኳስ እና ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች ለዚህ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ስፖርተኛው የኤ ሲ ኤል ጉዳት እንደገጠመው በተለያየ መልኩ የሚያውቅበት አጋጣሚ አለ፡፡ በቀዳሚነት ጅማቱ ሲበጠስ ድምፅ ሊያወጣ ስለሚችል በዛ ይታወቃል፡፡ በፍጥነት እብጠት ከታየም አንዱ መለያ ይሆናል፡፡ ስፖርተኛው ከጉዳቱ በኋላ መራመድ የማይችል ከሆነ የኤ ሲ ኤል ጉዳት የመሆን መጠኑ የሰፋ ነው፡፡
ዶክተር ሰይድ ሞሐመድ ከ ኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳነሱት የኤ ሲ ኤል ጉዳት እንደተከሰተ ለማወቅ የኤም አር አይ (MRI) ምርመራ ይደረጋል፡፡ ምርመራው ጉዳቱን ለመለየት ከ80 በመቶ በላይ እርግጠኛ የሚያደርጋቸው እንደሆነ ባለሞያው ተናግረዋል፡፡ ጉዳቱ ከተረጋገጠ በኋላ የህክምና ሂደቱን ለመጀመር የጉዳቱን መጠን ማወቅ ግድ ነው ያሉት ዶክተር ሰይድ በተለይ ፕሮፌሽናል ስፖርተኛ ከሆኑ የተበጠሰውን ጅማት ለመጠገን ቀዶ ህክምና ማድረጉ የተሸለ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሁሉም የኤ ሲ ኤል ጉዳቶች ቀዶ ህክምና ሊደረግላቸው አይችልም ፤ የጉዳቱ መጠን ፣ ጉዳት የደረሰበት ሰው እድሜ ሌሎች ጉዳዮችም ከግምት መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ ህክምናው ከተከናወነ በኋላ ወደ ሙሉ እንቅስቃሴ ለመምጣት ባለሞያው የሚሰጠውን እርዳታ መከተል አስፈላጊ እንደሆነ ዶክተር ሰይድ ይመክራሉ፡፡ ጉዳት የገጠመው ስፖርተኛም ይሁን ሌላ ግለሰብ በህክምና ሂደቱ እርዳታ ታግዞ ከዘጠኝ እስከ 12 ወር ቆይታ በኋላ ወደ ሙሉ እንቅስቃሴ የመመለስ እድል እንዳለው ዶክተር ሰይድ ሞሐመድ ተናግረዋል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ