በመዲናዋ በ26 የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ከ36 ሺህ 600 በላይ የዕለት ጉርስ የሌላቸው ወገኖች በቀን አንድ ጊዜ የምገባ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸዉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ኤጀንሲ የምገባ መርሃ ግብሩን ለደገፉና ስኬታማ እንዲሆን የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የከንቲባ ጽህፈት ቤት የተጠሪ ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ ዳዲ ሆርዶፋ (ዶ/ር)፣ የከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቶችን በማስተባበር የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሰው ተኮር ስራዎች ላይም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ውጤታማ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
በትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ያለው የተማሪ ምገባ መርሃ ግብር ለወላጆች እፎይታ የፈጠረ፣ በትምህርት ጥራትና በተማሪ ውጤታማነት ላይም አበረታች ውጤት ያስገኘ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ይህ ውጤት የመጣው የከተማዋ ባለሃብቶችና የተለያዩ ተቋማት ባደረጉት ድጋፍ መሆኑን የጠቆሙት ዳዲ (ዶ/ር)፣ ይህ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጸዳለች ሚካኤል በበኩላቸው፣ ኤጀንሲው በአዲስ አበባና በሸገር ከተሞች የተማሪ ምገባ፣ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁስ እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በከተማዋ በተገነቡት የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ባለሃብቶችን በማሳተፍ ምንም ገቢ የሌላቸውን ወገኖች የምገባ አገልግሎት እየሰጠ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የምገባ ኤጀንሲው ከቅድመ አንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ከ840 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን እየመገበና ከ1 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ተማሪዎች ደግሞ የደንብ ልብስ እና የትምህርት ቁሳቁስ እያቀረበ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በ26 የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት፣ ከ36 ሺህ 600 በላይ የዕለት ጉርስ የሌላቸው ወገኖችን በቀን አንድ ጊዜ እየመገበ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በዕለቱ በተካሄደ የዕውቅናና ሽልማት መርሃ ግብር የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባለሃብቶች እና ግለሰቦች ተካተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተማሪ ምገባ መርሃ ግብር በአመት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ እየሰራ መሆኑም ተጠቅሷል።
በተማሪዎች ምገባ ስራ ላይ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ከ16 ሺህ በላይ ወላጅ እናቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ስለመሆናቸውም በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል።
በምትኩ ተሾመ