በቀጣይ የአዲስ ዓመትን መግባት ተከትሎ ለሚከበሩ በዓላት ከ3.2 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለግብይት ማዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ንግድ ስራዎች ድርጅት አስታወቀ፡፡
ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የፍጆታ ምርቶች ፍላጎት የሚጨምርባቸው በዓላትን ምክንያት በማድረግ የምርት እጥረትና የዋጋ መናር እንዳይከሰት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቂ መጠን ያለው ምርት ወደ መዲናዋ እንዲገባ ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡
ምርትን ወደ መዲናዋ በስፋት ከሚያስገቡ ተቋማት መካካል አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ ንግድ ስራዎች ድርጅት፣ በምርት አቅርቦት ሂደቱ ላይ እያከናወነ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ቅኝት አድረጓል፡፡

የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አሰፋ፣ ከፊታችን ለሚከበሩ በዓላት ከ3.2 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይትን ጨምሮ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች በበቂ ሆኔታ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ምርቶቹን ቤት ለቤት እና በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት በተመጣጣኝ ዋጋ ለመዲናዋ ነዋሪዎች እንዲደርሱ እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ፣ የምርት አቅርቦትን በማስፋት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በሰራቸው ስራዎች ውጤት ተገኝቷል ያሉት አቶ መስፍን፣ በግብይት ሰንሰለት መርዘም ምክንያት ይደርስ የነበረውን አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እያስቀረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በቴዎድሮስ ይሳ