የ41ኛው የአፍሪካ ትምህርትና ምዘና ጉባኤ በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው። ከተማዋን አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ዘርፈ ብዙ ለውጦች እየተመዘገቡም ይገኛል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ በተሰራው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራ ለውጡ በጉልህ የሚታይ እንዲሁም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ መሆን እንደሚችል የ41ኛው የአፍሪካ ትምህርትና ምዘና ጉባኤ ተሳታፊዎች ምስክር ናቸው፡፡ ስራው ከተማዋን ዘመናዊ ከማድረጉም በተጨማሪ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻና የአለም አቀፍ ሁነቶች የስህበት ማዕከል እያደረጋት መሆኑ በብዙዎች ተመስክሮላታል፡፡

በጉባዔው ለመሣተፍ ከዛንቢያ የመጡት ሳደረኪን ኮያ፤ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ከተሞች በፍጥነትና በጥራት እያደጉና እየተለወጡ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ሁለተኛ ቤቴ በምቆትራት አዲስ አበባ፤የተሰራው ዘርፈ ብዙ ስራ ከተማዋን ብቁ የአፍሪካ መዲና መሆኗን የሚመሰክር ብቻም ሳይሆን ለሌሎችም ሀገራት ምሳሌ መሆን የሚችል ነው ብለዋል፡፡
መዲናዋ አለም አቀፍ ሁነቶችን ለማሰናዳት የሚያስችል ሙሉ ቁመና ላይ መሆኗን የገለፁት ደግሞ አቦ ቤከም (ፕ/ር) ከካሜሮን የመጡ ሌላኛው የከተማዋ እንግዳ ናቸው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የነበረችው አዲስ አበባና ያሁኗ ሰፊ ልዩነት እነዳላቸው ገልፀው፤ በተለይም በጽዳትና በመሰረተ ልማት የተሰራው ስራ የከተማዋን ከፍታ የሚያሳይ ብቻም ሳይሆኑ ስራውን ውጤታማ ካደረጉ ድንቅ መሪዎች የአህጉሪቱ መሪዎችም ተሞክሮ ሊወስዱ የሚገባ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የትላንት ታሪኳን በጠበቀ መልኩ ተሰናስለው የተሰሩ መሰረተ ልማቶች በተለይም የአንድነት ፓርክና ሌሎች የለሙ ስፍራዎች የሚታይ ለውጥና ውበትን ለከተማዋ አጎናጸፏታል ያሉት ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ የመጡት ማፍ ራኮሜሱ (ዶ/ር) ናቸው። የጉባዔው ተሣታፊዎች የከተማዋ ፈጣን ለውጥ ብቻም ሳይሆን የቀደመ ታሪኳን በጠበቀ መልኩ የተሰራበት ጥበብም አስደናቂና ልምድ የሚወሰድበት መሆኑ አብራርተዋል፡፡
41ኛው የአፍሪካ ትምህርትና ምዘና ጉባኤን በተሳካ ሁኔታ እያካሄደች የምትገኛው የአዲስ አበባ ከተማ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ150 በላይ አህጉርና አለም አቀፍ ሁነቶችን በማስተናገድ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ስህበት መሆኗን ለአለም እየገለጠች ትገኛለች፡፡
በሚካኤል ህሩይ