ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ረገድ አበረታች ስኬቶች ማስመዝገቧን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ወ/ሮ አለምፀሃይ ጳውሎስ ገለፁ።
የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የመከላከል ቡድን 50ኛ የከፍተኛ አመራሮች ግብረ-ኃይል ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ ከነሐሴ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር የመከላከል ቡድን ዓመታዊ ጉባኤ እንደቀጠለ ነው።
የዓመታዊ ጉባኤው አካል በሆነውና በዛሬው እለት በተጀመረው የቡድኑ 50ኛ የከፍተኛ አመራሮች ግብረ-ኃይል ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ወ/ሮ አለምፀሃይ ጳውሎስ፤ ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ረገድ አበረታች ስኬቶች ማስመዝገቧን ለተሳታፊዎቹ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ፤ ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ብሎም በቀጣናው ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ስትራቴጂ ነድፋ እየሰራች መሆኑን አስገንዝበዋል።
ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን፣ በህገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ መጠቀምን እንዲሁም ሽብርተኝነትን መደገፍን በጋራ ለመከላከል ቀጠናዊ ትብብሮችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ተገልጿል።
ከጉባኤው ባሻገር የፎረሙ ተሳታፊዎች በቆይታቸው በቡድንና በተናጠል አዲስ አበባን እየጎበኙ እንደሚገኙ ለኤ.ኤም.ኤን ገልፀዋል።
አዲስ አበባ የአለማችን 3ኛዋ ግዙፍ የዲፕሎማሲ ከተማና የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ፤ ይህን የሚመጥን የከተማ ልማትና የመሰረተ ልማት ግንባታ ውስጥ መግባቷን በአድናቆት እንደተመለከቱም ተናግረዋል።
በቀጠለው ጉባኤ የፋይናንስ 1 አባል ሀገራት በፋይናንስ ደህንነት ተቋማት የተወከሉበት የቀጠናው ቡድን ጉባዔ ከነገ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
ቡድኑ ሶስት ዓበይት ጉባኤዎች ያሉት ሲሆን፤ 25ኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባዔ ከመክፈቻው እለት ጀምሮ ተካሂዷል።
በቀጣይ እስከ ነሃሴ 24 በሚዘልቀው ስብሰባ 8ኛው የመንግስትና የግል አጋርነት ምክክር ፎረም እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
በይታያል አጥናፉ