የአዲስ አበባ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን “ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎነት” በሚል መሪ ሀሳብ ለበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
በስልጠና መድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ የህብረተሰብ ተሳትፎ በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይመር ከበደ፣ ወጣቶች ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ አላማ በማዋል ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የስልጠናው አላማ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በመከላከል እውነተኛ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ ማድረስ እንዲቻል ግንዛቤ ማስጨበጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ በዲጂታል ዘመን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን አወንታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆን እንደሚገባውም አሳስበዋል።
በስልጠናው የተሳተፉ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በበኩላቸው፣ ስልጠናው በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ክህሎትን የሚያዳብሩበት እና አቅማቸውን የሚያሳድጉበት እንደሚሆን ተናግረዋል።
በጎ ፍቃደኛ ወጣቶቹ አክለውም፣ ስልጠናው ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ አላማ በማዋል ረገድ ግንዛቤ የጨበጡበት እንደሆነም ገልጸዋል።
በመሀመድኑር አሊ