በበረዶ ዘመን መጠናቀቂያ ከ8 ሺህ 500 አመት በፊት ጠፍቶ እንደነበረ የሚነገርለትን ከተማ ማግኘታቸውን አርኪኦሎጂስቶች ተናግረዋል።
በዴንማርክ ባህር ዳርቻ የተገኘው ከተማ በበረዶ መቅለጥ የተነሳ በሚከሰት የባህር ከፍታ መጨመር የተነሳ ሳይሰምጥ እንዳልቀረ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በቁፋሮ መውጣት የቻለው ጥንታዊ የከተማ ክፍል 430 ስኩየር ጫማ ስፋት ያለው ስፍራ ሲሆን፥ አርኪኦሎጂስቶች በባህር ውስጥ እያደረጉት ባለው ቁፋሮ ተጨማሪ የከተማውን ክፍል ለማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
በቁፋሮ በተገኘው የከተማ ክፍል ውስጥ የተደራጀ የሰዎች ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንደነበር ምልክቶች ተገኘተዋል።
በተጨማሪም ከድንጋይ የተሰሩ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ የቀስት ጫፍ ፣ የእንስሳት አጽሞች እና ሌሎችም በእድገት ሂደት ላይ የነበረ ማህበረሰብ በስፍራው ይኖር እንደነበረ ጠቋሚ ምልክቶች መኖራቸውን ነው ተመራማሪዎቹ የገለጹት።
አርኪኦሎጂስቶቹ በከተማዋ የተገኘው ስልጣኔ በእድሜ እና በውሀ ሳይበላሽ አየር በሌለበት ቦታ ይህን ያህል ሽህ አመታት መዝለቁ “ጊዜ በዚህ ስፍራ ቆሞ ነበር” እንዲሉ አድርጓቸዋል።
ከዚህ ቀደም በምድር ውስጥ ጠፍተው የነበሩ የድንጋይ ዘመን ከተሞች በተደጋጋሚ የተገኙ ሲሆን፥ በባህር ውስጥ ሲገኝ ግን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሲል ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት አስነብቧል።
ተመራማሪዎች 15 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ፈንድ የተበጀተለት የጠፉ ከተሞችን የማፈላለግ አለም አቀፍ ፕሮጀክት ላይ ለአመታት ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ።
ለ6 አመታት የሚቆየው አለም አቀፍ ፕሮጀክት በባልቲክ እና በሰሜን ባህር የጠፉ ጥንታዊ ከተሞችን ማፈላለግ ላይ ትኩረት አድርጓል።
በዳዊት በሪሁን