ሰዎችን ከአደጋ መታደግ ደሞዙ የሆነው በጎ-ፍቃደኛ

You are currently viewing ሰዎችን ከአደጋ መታደግ ደሞዙ የሆነው በጎ-ፍቃደኛ

‎AMN ነሀሴ 21/2017 ዓ.ም

‎አካል ጉዳተኛ መሆኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከመስጠት እንዳላገደው ያስረዳል በጎ-ፍቃደኛው ወጣት። ‎”የኔ ደሞወዝ አንድ ሰውን ከትራፊክ አደጋ መታደግ ነው” ሲል አካል ጉዳተኝነቱ ያልበገረው የመንገድ ፍሰት ደህንነት ተቆጣጣሪ (የትራፊክ ረዳት) በመሆን እያገለገለ የሚገኘው ወጣት ይናገራል። እግሮቹ ላይ ጉዳት በመኖሩ በእጆቹ እየተጓዘ የትራፊክ ፍሰቱን ማሳለጥ የሁልጊዜ ተግባሩ አድጎታል፤ ወጣት ሰኚ ከበበ።

‎በሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ ወዴሳ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ሰኚ፣ አስፓልት የሚሻገሩ ዜጎችን የትራፊክ ደንቦችን አውቀውና ጠብቀው እንዲጓዙ ማስተባበር እና ማስተማር የዘወትር ስራው ነው። ‎ስልክ እያወሩ፣ በዣንጥላ ተከልለው የእግረኛ መንገድ የሚያቋርጡ መንገደኞችን ህይወት ከአደጋ መታደግ የየቀን ተግባሩ እንደሆነ ይገልፃል።

‎በመንገድ ፍሰት ድህንነት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መሰማራቱን ያዩ መንገደኞች በስራው ተገርመው ለሚጠይቁት ጥያቄ የሁል ግዜ መልሱ፤ የሰው ህይወትን ከትራፊክ አደጋ መታደግ ከምንም በላይ እርካታ እንደሚሰጠው ነው። ወጣት ሰኚ አካል ጉዳተኝነቱ ሳይበግረው ከአንድ አመት በላይ በመንገድ ፍሰት ደህንነት ሥራ በመሰማራት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት አበርክቶ አድርጓል። ይህንን በማድረጉም ዜጎች ለትራፊክ አደጋ እንዳይጋለጡ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ደስታ በተሞላበት አገላለፅ ተናግሯል።

‎የአካል ጉዳት እያለበት ይህን ለማድረግ ምን አስቸገረው? የሚሉት በርካቶች ቢሆኑም፣ ወጣት ሰኚ የሚሰጠው ነጻ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርካታን እንደሚሰጠው ይናገራል። ወጣት ሰኚ የትኛውንም ሰራ ለመስራት ወደ ኋላ እንደማይል ገልጾ ፤ ከዚህ ቀደም “ድንጋይ ፈልጬ አውቃለሁ” በማለት ለስራ ያለውን ፍቅርና ብርታት ይናገራል። “ቁጭ ብዬ ከምለምን” የትኛውንም ስራ ለመስራት ሁሌም ዝግጁ ነኝ ሲል ቁርጠኝነቱንም ገልጿል።

‎ወ/ሮ መክሊት አየለ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው። ስለ ወጣቱ ሲያስረዱ ፣ አካል ጉዳተኝነቱ ሳይበግረው ህብረተሰቡን በታማኝነት እና በቁርጠኝነት በበጎ ፈቃድ እንደሚያገለግል ይመሰክሩለታል። ወጣት ሰኚ የአየር ፀባዩ ሳይበግረው የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ወጣት ሰኚ የመንገድ ፍሰትን የሚያሳልጥበት ቦታ የትራፊክ ተቆጣጣሪ የሆኑት ሳጅን መኮንን ጉተታ ስለ ወጣቱ ትጋት ሲናገሩ፣ ሰኚ የትራፊክ ድህንነት በማስተባበር የትራንስፖርት ፍሰት በሚበዛበት ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

‎‎ዝናብ ፣ብርድ፣ ፀሃይ እና ሙቀት ሳይበግረው ቀን እና ሌሊት ሳይል እያገዛቸው እንደሚገኝ ሳጅን መኮንን አስረድተዋል። በዚህ የበጎ ፈቃድ ተግባሩ ያመሰገኑት ሳጅን መኮንን፣ ሌሎች ሰዎችም ከሰኚ ተምረው በተሰማሩበት የሥራ መስክ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ወጣቱ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review