ሰው ሰራሽ አስተውሎቶች መረጃዎችን የሚያገኙት ከየት ነው?

You are currently viewing ሰው ሰራሽ አስተውሎቶች መረጃዎችን የሚያገኙት ከየት ነው?

‎AMN – ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም

የአሁናዊው አለም ቀዳሚ መነጋገሪያ የሆነው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ.አይ) መልኩን እና አገልግሎቱን እየቀያየረ የሚገባበት ዘርፍ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከተ ይገኛል።

በወታደራዊ ፣ ትምህርት እና ጥናት ፣ ህክምና ፣ ቴክኖሎጂ እና ሌሎችም ዘርፎች በአሁኑ ወቅት ሰው ሰራሸ አስተውሎት በሰፊው ከገባባቸው ዘርፎች መካከል ይጠቀሳሉ። በመዝናኛው አለምም የግጥም እና የፊልም ሀሳብን በመስጠት ብቻ ሙዚቃ እና ፊልምን ጥንቅቅ አድረገው የሚያቀርቡ ሰው ሰራሽ አስተውሎቶች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።

እንደ ቻት ጂፒቲ እና ኦፕን ኤ አይ ፣ የቻይናው ዲፕ ሲክ እንዲሁም የጎግሉ ጀመናይ በርካታ ተጠቃሚ ያላቸው ቻት ቦት ኤ.አይ ናቸው። ሰው ሰራሽ አስተውሎቶች በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ሰዎች ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች የሚሰጧቸውን ምላሾች የሚያገኙት ከየት ነው የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ስታቲስታ በዚህ ዙሪያ ይዞት በወጣው የስታትስቲክስ መረጃ ሰው ሰራሽ አስተውሎቶች ከመንግስት እና ከጥናት ተቛማት የመረጃ ቛቶች ጀምሮ የተለያዩ በኢንተርኔት ላይ የሚገኙ መረጃዎችን እንደሚቃኙ ጠቁሟል። ሰው ሰራሽ አስተውሎቶች መረጃዎችን የሚያገኙት ከየት ነው? በሚል በቀረበው ሪፖርት ቀዳሚ የመረጃ አማራጭ ሆነው የተገኙት ማህበራዊ ትስስር ገጾች እንደሆኑ ተመላክቷል።

በዚህም ሬዲት በ40.1 በመቶ የ ኤ.አይ የመረጃ ምንጭ በመሆን በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፥ ዊኪፒዲያ በ26.3 በመቶ ሁለተኛ ፣ ዩትዩብ 23.5 በመቶ ሶስተኛ እና ጎግል 23.3 በመቶ አራተኛ የመረጃ ምንጭነትን በመሸፈን በደረጃ ተቀምጠዋል። በ2025 በአለም አቀፍ ደረጃ የሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን ለማበልጸግ እና ለሌሎች አገልግሎቶች ከ 375 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ይደረጋል።

በ2028 ይህ የገንዘብ መጠን ወደ 632 ቢሊየን ዶላር እንደሚያድግ የኢንተርናሸናል ዳታ ኮርፖሬሽን መረጃ ይጠቁማል። የኤ.አይ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ የሆኑት ገጾች የትኞቹ እንደሆኑ ከስር ካለው ምስል ይመልከቱ።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review